“የግጭት ቀጣና በነበረ አካባቢ ችግኝ መትከል ልዩ ትርጉም አለው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

16

ባሕር ዳር: ሐምሌ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ክልላዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን በሰሜን ጎጃም ዞን ይልማና ዴንሳ ወረዳ በአቦላ ተራራ አስጀምረዋል።

በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ርእሰ መሥተዳድሩን ጨምሮ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር) ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የአካባቢው ምልክት በኾነው አቦላ ተራራ ላይ የአረንጓዴ አሻራችንን አሳርፈናል ነው ያሉት። የክልሉ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር መበሰሩንም ተናግረዋል። የዛሬ ዓመት አካባቢው ግጭት እንደነበረበት የተናገሩት ርእሰ መሥተዳድሩ የእኛ ፍላጎት የግጭት ቀጣና ማድረግ የሚፈልጓቸውን አካባቢዎች የልማት ቀጣና ማድረግ ነው ብለዋል።

“የግጭት ቀጣና በነበረ አካባቢ ችግኝ መትከል ልዩ ትርጉም አለው” ነው ያሉት። እስካሁን ድረስ ብዙ ተክለናል፣ መራቆትን ለማስቀረት ጥረት አድረገናል፣ አሁን ደግሞ ከአረንጓዴ አሻራ ጥቅሞች መካፈል አለብን ብለዋል።

በሥራችን ውጤት ዓለም መስክሯል ነው ያሉት። የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የአንድ ቀን ሥራ አይደለም፣ የአንድ ተቋም ሥራም አይደለም፣ ሥራው ዘላቂ እና በቅንጅት የሚሠራ ነው ብለዋል። ከረሃብ እና ከድርቅ የምንላቀቅበት ሥራ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ችግሩን ለመቅረፍ በቅንጅት እና በዘላቂነት መሥራት አለብን ነው ያሉት። የአረንጓዴ አሻራ በምጣኔ ሀብት የሚኖረው ጥቅም ትልቅ መኾኑን ተናግረዋል።

የሰው እና የተፈጥሮን የተዛባ ግንኙነት ለማስተካከል የአረንጓዴ አሻራ ሥራን ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በየደረጃው የሚገኙ መሪዎች፣ ባለሙያዎች እና ሕዝቡ ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ ጠይቀዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የቆዬውን ችግር ለመፍታት የሚያስች መኾኑን በመረዳት መሥራት ይጠበቃል ብለዋል። ግብርና ሚኒስቴር እያደረገ ላለው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች የተተከለውን ችግኝ እንዲንከባከቡ አሳስበዋል። ተጨማሪ ችግኞችን በማሳቸው እንዲተክሉ አስገንዝበዋል። የአማራ ክልል ሰላም እየተሻሻለ መጥቷል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ሰላምን እያረጋገጥን፣ ልማትን የበለጠ እያሰፋን እንሄዳለን ብለዋል። ለዚህ ደግሞ በትኩረት እንደሚሠራ ነው ያመላከቱት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ ስኬታማ እንዲኾን ወጣቱ በጉልበቱ፣ ባለሃብቱ በገንዘቡ ድጋፍ ማድረግን ይጠይቃል።
Next article“የበጎ ፈቃድ ሥራው ከችግሬ አውጥቶኛል” ቤታቸው የተጠገነላቸው እናት