
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 24/2012 ዓ.ም (አብመድ) ከሱዳን የሚገቡ ዜጎች ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚሄዱ በመሆናቸው ሳይመረመሩ ካለፉ ወረርሽኙን በከፍተኛ ደረጃ ሊያስፋፉት እንደሚችሉ የኅብረተሰብ ጤና ስፔሻሊስት ዶክተር አስገንዝበዋል፡፡
አካባቢውን ‘‘የነጭ ወርቅ ምድር’’ ይሉታል፤ የሰሊጥ ወርቅ ይታፈስበታል፤ ምዕራብ ጎንደር ዞን፡፡ አሁን ደግሞ የኮሮናቫይረስ ከፍተኛ ስጋት ደቅኖበታል፤ በእርግጥ ስጋቱ በዞኑና በክልሉ ተወስኖ የሚቀር ይደለም፡፡ ምክንያቱም ስጋቱን ከፍ ያደረጉት ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ከመላው የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ ዜጎች ናቸውና፡፡ ዜጎቹ በኃላፊነት ስሜት ወደ ለይቶ ማቆያ ካልገቡና ተመርምረው ነጻ መሆናቸውን ሳያረጋግጡ ወደ መላ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚቀላቀሉ ከሆነ ደግሞ የሥርጭቱን ፍጥነትና ሥፋት አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ በምዕራብ ጎንደር ዞን ከነዋሪዎች ያልተናነሱ የዕለት ጉርስ ፈላጊዎችም በተለይ የክረምቱን የእርሻ ወቅት ምክንያት በማድረግ ይጎርፉበታል፤ ይህ ደግሞ ከወቅቱ የኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የስጋት ቀጣና አድርጎታል፡፡
እናም በአካባቢው ያለው ስጋት በፍጥነት ገደብ ካልተበጀለት ወረርሽኑ ወደገጠሩ ኅብረተሰብ እንዲገባ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ሕይወትን ለመደጎም ወደአካባቢው የሄደው የቀን ሠራተኛ ወደቀዬው ሲመለስ በጥንቃቄ የተቀመጡ ቤተሰቦቹን በቫይረሱ ሊያስይዛቸውም ይችላል፡፡ እነዚህ በሮች ከየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የሚመጣውን ኢትዮጵያዊ የሚያስገቡና የሚያስወጡ በመሆናቸው ከፀጥታ ኃይሉ ዕይታ ውጭ የገባ አንድ ኢትዮጵያዊ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን የማዳረስ ዕድል ይኖረዋል፡፡
የኅብረተሰብ ጤና ስፔሻሊስቱ ዶክተር መኮንን አይችሉህም በቅርብ በኢትዮጵያ እየታዩ የመጡ የኮሮና ቫይረስ ውጤቶች በሽታው በፍጥነት እየተስፋፋ እንደሆነ የሚያሳዩ፣ ወረርሽኙም በማኅበረሰቡ ውስጥ መግባቱን የሚያመላክቱ መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ወረርሽኙ በፍጥነት እየተሠራጨ ያለና በሌሎች አገሮች የሚታዬው ጉዳት ወደዚህም ሊመጣ እንደሚችል አመላካች መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የአማራ ክልል በሰፊ ኪሎ ሜትር ከሱዳን ጋር የሚዋሰን መሆኑ ስጋቱ ከፍ ያለ መሆኑን በማንሳትም በድንበር አካባቢ የሚገባውና የሚወጣው ሰው ሕጋዊ አለመሆን ቁጥጥሩን አዳገች እንዳያደርገው ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ ነው ያስረዱት፡፡ ‘‘በሕገ ወጥ መንገድ ከሚገቡት ሰዎች መካከል አንደኛው ቢያዝ አብረው የሚጓዙትን በቀላሉ በቫይረሱ ያስይዛል፤ እነዚህ ወደ ማኅበረሰቡ ሲቀላቀሉ ደግሞ በፍጥነት ያሠራጩታል’’ ነው ያሉት ዶክተር መኮንን፡፡ ይህ ደግሞ እንደ ድርና ማግ የተሳሰረውን ማኅበረሰብ ለይቶ ለማወቅና በሽታውን ለመቆጣጠር አዳጋች እንዳያደርገው ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህን አደገኛ ስርጭት ለመመከት ከሱዳን በኩል የሚገቡትን ሰዎች መለዬትና መቆጣጠር ተቀዳሚው ሥራ መሆን እንዳለበት ዶክተር መኮንን መክረዋል፡፡ በአካባቢው ከቀበሌው ጀምሮ እስከ ፌደራል ድረስ በከፍተኛ ቅንጅት መሥራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ ቁጥጥሩም በታወቁ የመግቢያ በሮች ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም አካባቢዎች መሆን እንዳለበትና ለዚህም ማኅበረሰቡ በኃላፊነት ስሜት ተባባሪ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ አደባባይ ሙሉጌታ የዞኑ ሦስት ወረዳዎች 17 ቀበሌዎችና አንድ ከተማ አስተዳደር ከሱዳን ጋር እንደሚዋሰን ገልጸዋል፡፡ የአካባቢውን ሚሊሻዎች ስልጠና ሰጥተው በማሰማራት በድንበሩ አካባቢ ቁጥጥር ለማድረግ እየሞከሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ በዞኑ 741 ሰዎች በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንደሚገኙ የገለጹት አቶ አደባባይ ለ494 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎ የዛሬን ሳይጨምር 54 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶበቸዋልም ብለዋል፡፡ በሱዳን አዋሳኝ 19 በሮች እንዳሉ በመግለጽም ቢያንስ በዘጠኙ ለይቶ ማቆያ እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡ ዞኑ የመመርመሪያ እና የታማሚዎች ለይቶ ማከሚያ እንደሚያስፈልገው ጥያቄ ቀርቦ የክልሉ መንግሥትም ለጉዳዩ ትኩረት እንደሚሰጥ መግለጹ ይታወሳል፡፡ ዋና አስተዳዳሪው በምግብ አቅርቦት፣ የውኃውን ችግሩን ለመፍታት በመሥራትና በሌሎችም የክልሉ መንግሥት እያደረገ ያለው ድጋፍ አበረታች መሆኑን አንስተዋል፡፡
የፌደራል መንግሥት ግን ወደስፍራው እየሄደ ጉብኝት ቢያደርግም እስካሁን ድረስ ተጨባጭ ድጋፍ አለማድረጉን ተናግረዋል፡፡ በመመሪያው መሠረት በለይቶ ማቆያ በ20 ክፍሎች 80 ሰዎችን መያዝ እንደሚቻል ያነሱት አቶ አደባባይ አሁን ላይ ግን በ20 ክፍሎች ከ300 በላይ ሰዎች በጥግግት እንደሚኖሩ አስታውቀዋል፡፡ ከሱዳን የሚመጡ ኢትዮጵያውን በቀጥታ ከኢንቨስተሮች መጠለያ መቀላቀል መከላከሉን ከባድ እንዳደረገውም ገልጸዋል፡፡ ይህም ወደ ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን በሽታውን ይዘው እንዲመለሱ እንዳያደርግም ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
አካባቢው ለአገር የሚያመጣውን አደጋ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የፌዴራል መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ማቅረብ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
በአካባቢው ወደ ለይቶ ማቆያ የሚገቡት ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ዜጎች በመሆናቸው የጤና ሚኒስቴር በአካባቢው የለይቶ ማቆያ በግንባት፣ የሕክምና ግብዓትና ምግብ በማቅረብ ማገዝ እንዳለበትም ነው የጠየቁት፡፡ ከሱዳን መንግሥት ጋር በመነጋገር ከዚያ የሚመጡ ዜጎች እየተመረመሩ የሚመጡበትን፤ ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን የሚመለሱትም እየተመረመሩ የሚሄዱበትን መንገድ ቢያመቻችም በሽታውን ለመቆጣጠር አጋዥ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
የፌዴራል መንግሥት ትናንት በሰጠው መግለጫ ደግሞ ምዕራብ ጎንደር ዞንን ጨምሮ በጠረፍ አካባቢዎች ወረርሽኙን ለመከላከል ለሚደረገው ሥራ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ማስታወቁ አሳውቋል፡፡
ዘጋቢ፡-ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡
