
ደሴ: ሐምሌ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደሴ ከተማ አሥተዳደር የ2017 ዓ.ም የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ 6 መቶ እናቶች በእንጀራ መጋገር ሥራ ተሰማርተው በኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው ሸድ ግንባታ ተጀምሯል። በጽዳት ዘመቻ እና በደም ልገሳም በርካቶች እየተሳተፉ ነው።
በበጎ ፈቃድ መርሐ ግብሩ ባለሃብቶችን በማስተባበር ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጪ የእንጀራ መጋገሪያ ሸድን በመገንባት እናቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑ ተመላክቷል።
የእንጀራ መጋገሪያ ሼድ የሚገነባው የወረታ ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ግሩፕ የሰንሰዋ ትሬዲንግ ወኪል በኾኑት ተመስገን አረጎ ነው። ግንባታውን ለማከናወን ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መድቦ ለመሥራት መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ለአቅመ ደካማ እና አረጋውያን ደረጃውን የጠበቀ የመኖሪያ ቤት ለመገንባት በእቅድ ተይዞ እየተሠራ መኾኑንም የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ገልጸዋል።
ለተግባሩ ስኬታማነት ወጣቱ በጉልበቱ፣ ባለሃብቱ በገንዘብ ድጋፍ በማድረግ በቅንጅት ይሠራል ብለዋል።
የበጎ ፈቃድ ተግባራትን ልምድ በማስፋትና ካለፉት ዓመታት ተሞክሮ በመውሰድ የተጀመሩ ሥራዎችን ማሳካት እንደሚገባም የአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ጥላሁን ሽመልስ ተናግረዋል።
በበጎ ተግባር መሳተፍ አብሮነትን ያጠናክራል ፍቅርን ይጨምራልም ብለዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ሰይድ አራጋው የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በ17 የትኩረት መስኮች ከ131 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች ይሳተፉበታል ነው ያሉት።
በዚህም 114 ሚሊዮን ብር የሚገመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች እንደሚከናወኑ ነው የገለጹት።
ዘጋቢ:- ፊኒክስ ሀየሎም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!