
ፍኖተ ሰላም፡ሐምሌ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎጃም ዞን በ2017 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ114 ሚሊየን በላይ የደን፣ የአትክልት እና የፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል እየተሠራ መኾኑን የዞኑ ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ አጉማሴ አንተነህ ተናግረዋል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በርብርብ እየተሳተፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የሚተከሉ ችግኞች የሚፈለገውን ጠቀሜታ እንዲሰጡ በተከላ መርሐ ግብሩ ላይ እየተደረገ ያለውን ርብርብ በእንክብካቤው ላይም ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ ከ569 ሺህ በላይ የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል እየተሠራ መኾኑን የተናገሩት የፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ጊዜው ደግአረገ እስካሁን ከ200 ሺህ በላይ ችግኞች መተከላቸውን ተናግረዋል።
ከችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ጎን ለጎንም የችግኞች የእንክብካቤ ተግባራት እየተከናወኑ መኾኑንም አንስተዋል።
የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩን በውጤታማነት ለመፈፀም ከበጎ ፈቃድ ሥራው ጋር በማስተሳሰር እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
በተከላ መርሐ ግብሩ ላይ ሲሳተፉ አሚኮ ያገኛቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችም ችግኝ የሚያስገኘውን ሁለንተናዊ ጠቀሜታ ተረድተው እንክብካቤ እና ክትትሉ ላይ በንቃት እንደሚሳተፉም ነው የተናገሩት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን።