ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የአትክልት እና ፍራፍሬ ችግኞች እየተተከሉ ነው።

26

ጎንደር: ሐምሌ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ አሥተዳደር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የማስጀመሪያ ፕሮግራም ተካሂዷል።

በክልል አቀፍ ደረጃ ከሐምሌ አንድ ጀምሮ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እየተከናወነ እንደሚገኝ የገለጹት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኛው በከተማ አሥተዳደሩ የዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በልደታ ክፍለ ከተማ መጀመሩን ገልጸዋል።

በከተማ አሥተዳደሩ ከ4 ሚሊዮን በላይ የደን ዛፎችን ጨምሮ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች እንደሚተከሉም ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች ከ86 በመቶ በላይ የጽድቀት መጠን እንደነበራቸው የገለጹት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በዚህ ዓመት የሚተከሉት ከ95 በመቶ በላይ እንዲጸድቁ ይሥራል ብለዋል።

የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁና የአካባቢን ሥነ ምህዳር እንዲጠብቁ ለማድረግ ከማኀበረሰቡ ጋር በጋራ እንክብካቤ እንደሚደረግም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አሥረድተዋል። ከዚህ በፊት የተተከሉ ችግኞች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳስገኙና የአፈር መሸርሸርን ማስቀረታቸውንም ገልጸዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በየዓመቱ ለውጥ እያመጣ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን የኅዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጋሻው እሸቱ ናቸው።

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።

በጎንንደር ከተማ አሥተዳደር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ላይ ማኀበረሰቡ እያደረገ ያለው ተሳትፎ የሚበረታታ መኾኑን የገለጹት አቶ ጋሻው ጤናማ አካባቢን ለመፍጠር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።

በመርሐ ግብሩ የተገኙ የከተማዋ ነዋሪዎች በየዓመቱ በሚደረጉ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ችግኞችን ከመትከል ባለፈ እንዲጸድቁ በሚደረገው ተግባር ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

በዛሬው እለት በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከአምስት ሺህ በላይ የደን ዛፎችና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚያሰገኙ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች መተከላቸውንም የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ተፈጥሮ ሃብት ቡድን መሪ አቶ ቀናው አሰፋ አስታውቀዋል።

ዘጋቢ:–ኀይሉ ማሞ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከተማ አስተዳደሩ ከ10 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል አቅዶ እየሠራ ነው።
Next articleከችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ጎን ለጎን የእንክብካቤ ሥራዎችም እየተከናወኑ ነው።