
ባሕር ዳር: ሐምሌ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር በአራቱም ክፍለ ከተሞች የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ”በመትከል መንሰራራት” በሚል መሪ መልዕክት ተካሂዷል።
በአብማ ክፍለ ከተማ በተካሄደው ማስጀመሪያ መርሐ ግብር የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ስለሽ ሙሉነህ በየዓመቱ ችግኝ የምንተክለው የተፈጥሮ ሚዛንን ለመጠበቅ ያለው ዓላማ ከፍተኛ መኾኑን ስላረጋገጥን ነው ብለዋል፡፡
የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ ሥራዎች አጠናክሮ በማስቀጠል የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንሠራለን ነው ያሉት።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ መለሰ ሙላት በከተማው ባሉ አራቱም ክፍለ ከተሞች በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ከ2 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን እንደሚተከሉ ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች ለአካባቢ ጥበቃ ትልቅ ጠቀሜታ እየሰጡ መኾኑን ያነሱት ኀላፊው ማኅበረሰቡ በጋራ እና በግል ችግኞችን በመትከል እና በመንከባከብ ጥቅም እንዲሰጡ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
የሰው ልጅ ጤናማ ሕይዎት እንዲኖር እፅዋት ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ያሉት እና ችግኝ ሲተክሉ ያገኘናቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በተከታታይ ዓመታት በመሳተፍ እና ተፈጥሮን በመንከባከብ ተስማሚ አካባቢ ለመፍጠር የድርሻቸውን እያበረከቱ መኾኑን ተናግረዋል። የተተከሉ ችግኞችን ዘላቂ ለማድረግ እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡
በደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ10 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ከከተማ አስተዳደሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን