
ደብረማርቆስ፡ ሐምሌ1/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን እንደሚሠሩ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ አስታውቋል፡፡
በዞኑ የዜጎች የበጎ ፈቃድ አግልግሎት በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ተጀምሯል፡፡
በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በችግኝ ተከላ፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት በመጠገን እና በማደስ የደም ልገሳ እና ሌሎችንም ተግባራት በዕቅድ አካቶ የያዘ ነው፡፡
የዜጎች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከመልካም እሳቤ የሚመነጭ ተግባር በመኾኑ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ሕይዎት ሊለውጥ በሚችል መልኩ እየተሠራበት ይገኛል፡፡
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ቢሻው ሞላ በክረምቱ የዜጎች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ900 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚያሳትፍ እና ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭንም የሚታደግ ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
ወጣቶችም ከችግኝ ተከላ ባለፈ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠሩ ስለመኾናቸውም አብራርተዋል፡፡
በብልጽግና ፓርቲ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋየ በላይ በዞኑ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ችግር የሚፈቱ ተግባራት ላይ በጎ ፈቃደኞችን ለማሳተፍ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ወጣቶች የአቅመ ደካሞችን ቤት በመጠገን፣ በችግኝ ተከላ፣ በደም ልገሳ እና በሰላም እሴት ግንባታ መሳተፍ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን