“ኢትዮጵያ በዓባይ ውኃ አጠቃቀም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ ተፈጥሯዊ ካሳ የምትጠይቅበት ወቅት ነው፡፡” ፕሮፌሰር በላይ ስማኔ

187

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 24/2012 ዓ.ም (አብመድ) አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ይዛው የነበረውን የፀረ ሽብር እንቅስቃሴ ማለዘቧን ተከትሎ በዚህ ወቅት የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካዊ ዲፕሎማሲ ድርሳን ሲገለጥ የዓባይ ውኃ አጠቃቀም ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖ ይገኛል፡፡ የዓባይ ዲፕሎማሲ ጉዳይ ዘመናትን ተሻግሮ እየተንከባለለ የመጣ ነው፡፡ የተፋሰሱ ሀገራት የሕዝብ ቁጥራቸው ማሻቀቡ እና ድህነት የቀጣናው መለያ መምሰሉ ፍትሐዊ የውኃ ክፍፍል መኖር ከመቼውም ጊዜ በላይ የኅልውና ጉዳይ ሆኗል፡፡ እንደደቡብ ሱዳን ዓይነት አዲስ ሀገር መፈጠሩ ደግሞ የዲፕሎማሲ ሥራውን አስፍቶታል፡፡

በአንፃሩ የተፋሰሱ የታችኞቹ ሀገራት በተለይም ግብፅ ከአሮጌ አስተሳሰብ ላይ ተቸክላ መቆሟ ለዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ እልባት አልባ መሆን እንደምክንያት ይነሳል፡፡

አንድ ወቅት ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ የሚለው የዓባይ ውኃ አጠቃቀም ዲፕሎማሲ የሚሽከረከረውም በካይሮ መንግሥት ፍላጎት ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ በተለይም ለዓባይ ውኃ ገፀ በረከትነት ማኅፀን የሆነችው ኢትዮጵያ በዘመናት መካከል ከውስጥ የሚፈጠርባትን ቀጋ ምቹ አልጋ አድርጋ የምትጠቀመው ግብፅ ወቅት እያየች ተደጋጋሚ ተፅዕኖ ለመፍጠር ስትሞክር ተስተውሏል፡፡ የሆነውም እየሆነ ያለውም እውነት ይህ ነው፤ ግብፅ በዓባይ ውኃ አጠቃቀም ላይ ዘመንን የዋጀ አስተሳሰብ ላለመላበስ ስትውተረተር መመልከት አሁን የዘመኑ እውነት ሆኗል፡፡

“ከዚህ በኋላ የዓባይን ውኃ አጠቃቀም ዲፕሎማሲያዊ ምህዋር መዘወር የሚኖርባት ሀገር ኢትዮጵያ ናት” ያሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ጥናት እና ግብርና ልማት ተመራማሪና መምህሩ ፕሮፌሰር በላይ ስማኔ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ማተኮር ያለበትም ለዓባይ ውኃ በምታበረክተው የተፈጥሮ ሀብት ላይ ተመሥርታ ተመጣጣኝ ካሳ በመጠየቅ እንደሆነ ፕሮፌሰሩ ይመክራሉ፡፡

በ1955 (እ.አ.አ) ግብጽ እና ሱዳን በዓባይ ውኃ ላይ በደረሱት ስምምነት መሠረት በአስዋን ግድብ መሙላት ምክንያት ውኃ ወደኋላ ተመልሶ በሱዳን መሬት ላይ ቢተኛ ውኃው ለሚያርፍበት የሱዳን መሬት 15 ሚሊዮን የግብፅ ፓውንድ ካሳ ለመክፈል ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ ይህም በጥቁር ዓባይ 59 በመቶ፣ በተከዜ-አትባራ 13 በመቶ እና በባሮ አኮቦ-ሶባት 14 በመቶ በአጠቃላይ 86 በመቶ የዓባይ ውኃ ድርሻ ያላት ኢትዮጵያ ለምታበረክተው አስተዋፅኦ ካሳ መጠየቅ እንደምትችል የሚያሳይ ተገቢና ሕጋዊ ልምድ መሆኑን ፕሮፌሰር በላይ ገልጸዋል፡፡

‘‘የሦስቱ ሀገራት የዓባይ ውኃ አጠቃቀም ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በፍፁም እንዲገናኝ ኢትዮጵያ ዕድል መስጠት የለባትም’’ ባይ ናቸው ፕሮፌሰሩ፡፡ ከዚያ ይልቅ ለጥቁር ዓባይ የውኃ ድርሻ አስተዋፅኦ ያለው የጮቄ ተራራ፣ ለተከዜ አትባራ እና ለጣና ሐይቅ አስተዋፅኦ ያለው የጉና ተራራ እና ለባሮ አኮቦ-ሶባት የውኃ ድርሻ አስተዋፅኦ ያላቸው የባሌ ተራሮችን ብዝኃ ሕይወት በመጠበቅ ላይ ሦስቱ ሀገራት ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚኖርባቸው ነው ያመለከቱት፡፡

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ፕሮጀክትን እውን ካደረገችበት 2003 ዓ.ም ጀምሮ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ላይ በርካታ ሥራዎችን መሥራቷንና ከዚህም አልፋ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ መድረኮች የአፍሪካን ድምፅ በመወከል ጥረቶችን ማድረጓን ፕሮፌሰር በላይ አስታውሰዋል፡፡ እናም ጥረቱ ለጋራ ጥቅም በመሆኑ ኢትዮጵያን በመደገፍ ግብፅ እና ሱዳን አብረው መቆም እንዳለባቸው አብራርተዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ ከተማሪዎቻቸው ጋር ለጥናት ወደ ሱዳን ሄደው እንዳረጋገጡት ሱዳን በደለል የተሸፈኑ ሰፋፊ የእርሻ ማሳዎችን ለማፅዳት እስከ 20 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ታወጣለች፤ ግብፅም የአስዋን ግድብን ከደለል ለመታደግ እንዲሁ ተመሳሳይ መጠን ወጭ ታወጣለች፡፡ እንደ ፕሮፌሰር በላይ ሁለቱ ሀገራት ደለል ለማስወገድ ገንዘብ ወጪ ከሚያደርጉ የዓባይ ወንዝ ገባሮችን በትብብር ቢያለሙ እና ከአስዋን ግድብ ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ የውኃ ብክነትን ለሚከላከለው የኢትጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ድጋፍ ቢያደርጉ ይመረጣል፡፡ ኢትዮጵያም በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የምትሠራቸውን ሥራዎች በማሳየትና ለደለልና ድርቅ መቀነስ ያላቸውን ፋይዳ በማስረዳት የካሳ ክፍያ ከታችኞቹ የተፋሰስ ሀገራት ለመጠየቅ አጀንዳዎችን ብትቀርፅ እንደሚመረጥ ነው ፕሮፌሰር በላይ የሚመክሩት፡፡

ኢትዮጵያም ግብፅ በየጊዜው በምትቀያይረው አጀንዳ ከመጠመድ ወጥታ የራሷን አጀንዳ ማራመድ እንደሚኖርባት አሳስበዋል፡፡ ቀጣዩ የዓባይ ውኃ አጠቃቀም ዲፕሎማሲያዊ አጀንዳ ኢትዮጵያ በምታቀርበው የተፈጥሮ ሀብቷ ካሳ ላይ መመሥረት እንዳለበትም ፕሮፌሰር በላይ ስማኔ መክረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleየፊደል ገበታው አባት ጌታ ቀኝ አዝማች ተሰፋ ገብረሥላሴ
Next articleሳይመረመሩ ከሱዳን የሚገቡ ዜጎች መዳረሻቸው የተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በመሆናቸው ወረርሽኙን የማስፋፋት ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑን የኅብረተሰብ ጤና ስፔሻሊስት ዶክተር አሳሰቡ፡፡