
ገንዳ ውኃ፡ ሐምሌ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎንደር ዞን አሥተዳደር ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት ከጂ ኤን ኬ ቴክኖሎጁ ሶሉሽን ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ጋር በመተባበር የኢ-ትኬትንግ አገልግሎትን በገንዳ ውኃ ከተማ መነኾሪያ አስጀምሯል።
በማስጀማሪያ መርሐ ግብሩ የክልል፣ የዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ እያሱ ይላቅ የመንገድ ላይ ትራንስፖርትን ለማዘመን እና የማኅበረሰቡን ችግር ለመፍታት በትኩረት እየተሠራ እንደኾነ አስገንዝበዋል።
የኢ-ትኬትንግ አገልግሎት የትራንስፖርት አሠራሩን አንድ ደረጃ ከፍ ያደረገ ቴክኖሎጂ መኾኑን ተናግረው ቀጣይ ከዚህ በበለጠ ለመሥራት ድጋፍ እና ክትትል ያስፈልጋል ብለዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሙሉዓለም ታደሰ አዲሱ ሲስተም መንገዶኞችን ከተለያዩ አጨበርባሪዎች በመታደግ የትራንስፖርት ሂደቱን ለማዘመን ቴክኖሎጁው እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
አገልግሎቱ በይፋ መጀመሩ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ ባለፈ ማኅበረሰቡ ከትራንስፖርት እንግልት እና ያለአግባብ ከሚከፈል የታሪፍ ወጭዎች ይታደጋል ብለዋል።
የጂ ኤን ኬ ቴክኖሎጅ ሶሊሽን ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት የኢ-ትኬትንግ አገልግሎት አስተባባሪ ዳዊት ነብዩ የድርጅቱ ዓላማ የማኅበረሰቡን የትራንስፖርት ችግር በመፍታት በትክክለኛ ታሪፍ እንዲጓዙ የሚያስችል ቴክኖሎጂ መኾኑን አስረድተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን