ችግኞች ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጡ መንከባከብ እና መከታተል ይገባል።

17

ደብረማርቆስ፡ ሐምሌ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “በመትክል ማንሰራራት” በሚል መሪ መልዕክት የ2017 የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በምሥራቅ ጎጃም ዞን በአዋበል ወረዳ ተጀምሯል፡፡

በምሥራቅ ጎጃም ዞን የ2017 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በአዋበል ወረዳ ሐምሌ 1/2017 ዓ.ም ተጀምሯል፡፡

ከዚህ በፊት የተተከሉ ችግኞች የተፈጥሮ ሚዛንን መመለስ፣ የአፈር መሸርሸርን መከላከል፣ የተፋሰስ ልማትን ማጠንከር እና ለእንሰሳት መኖ ማዋል አስችለዋል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የሚሳተፍበት የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የግብርና ልማት ወደ ላቀ ደረጃ የሚሸጋገርበት ነው ብለዋል፡፡

ሥራው የደን ልማትን የሚያሻሽል፣ የመስኖ እና ውኃ ሃብትን የሚያጎለብት፣ ለትውልድም የሚሻገር ተግባር መኾኑን ገልጸዋል፡፡

የአማራ ክልል የኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ኤጀንሲ አማካሪ ኃይለ ልዑል ተስፋ የዞኑን የደን ሽፋን ለማሳደግ፣ የተፈጥሮ የአየር ንብረትን ለማስጠበቅ እና የምርት ዕድገትን ለማሻሻል በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ ችግኞችን ጥቅም እንዲሰጡ ማድረግ ከኅብረተሰቡ የሚጠበቅ ተግባር መኾኑን አስገንዝበዋል፡፡

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አበበ መኮንን ሐምሌ 1/2017 ዓ.ም የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በክረምቱ የሚቀጥል እና ኅብረተሰቡን በንቃት የሚያሳትፍ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

በዞኑ በሁሉም ወረዳዎች የተጀመረው የችግኝ ተከላ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል፡፡

በችግኝ ተከላው የተሳተፉ የኅብረተሰብ ክፍሎችም ችግኞችን በመንከባከብ ለጥቅም እንዲደርሱ ኀላፊነት አለበት ነው ያሉት፡፡

በሀገር መከላከያ ሠራዊት በምዕራብ እዝ የ403ኛ ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል አዘዘው መኮንን ልማት እንዲፋጠን ዕድገት እንዲመዘገብ እና ሰላም እንዲሰፍን ከችግኝ ተከላ ባሻገር የሰውን ልጅ ሕይወት ማስቀጠል ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

ኅብረተሰቡም ለሰላም እና ልማት ሊተባበር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በምሥራቅ ጎጃም ዞን በተያዘው ክረምት ከ228 ሚሊዮን በላይ ችግኝ እንደሚተከል ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን።

Previous articleበምሥራቅ ጎጃም ዞን ከ228 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል።
Next articleየኢ-ትኬትንግ አገልግሎት የትራንስፖርት አሠራሩን አንድ ደረጃ ከፍ ያደረገ ቴክኖሎጂ ነው።