በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከ228 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል።

14

ደብረ ማርቆስ: ሰኔ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዞኑ የ2017 በጀት ዓመት የግብርና ሥራዎች አፈጻጸም እና የቀጣይ ዘጠና ቀን እቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል። የምሥራቅ ጎጃም ዞን በ2017 በጀት ዓመት በሰብል ልማት እና በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ውጤታማ ተግባራት መፈጸሙን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ በየገዜው የሚከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሮች ውጤት እያመጡ ስለመኾናቸው ተናግረዋል። ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ እና በበጎ ተግባርም የሚሠራ በመኾኑ በዘጠና ቀን እቅድ በማካተት ኅብረተሰቡን ያሳተፈ ሥራ ይሠራል ብለዋል። ከአረንጓዴ አሻራ ባሻገር በክረምቱ የግብርና ሥራ ትኩረት የሚሰጠው የሰብል ልማት መኾኑን የጠቀሱት ዋና አሥተዳዳሪው የግብዓት አቅርቦት እና የማሳ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

የአርሶ አደሮችን ኑሮ ለማሻሻል እና ለማዘመን የሚያስችል የገጠር ኮሪደር እና መሠረተ ልማት በቀጣይ ትኩረት የሚሰጠው ተግባር ስለመኾኑም አቶ ኑርልኝ ተናግረዋል። በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ኤጀንሲ አማካሪ ኀይለልዑል ተስፋ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚቻለው የአረንጓዴ አሻራን በትኩረት እና በውጤታማነት ሲፈጸም መኾኑን ተናግረዋል።

በዘጠና ቀን የታቀዱ ተግባራት ሳይሸራረፉ መተግበር አለባቸው ያሉት አቶ ኀይለልዑል ለዚህ ተግባር የሥራ ኀላፊዎች በትጋት ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል። የሚተከሉ ችግኞችን ውጤታማ ማድረግም ከሁሉም ባለድርሻ የሚጠበቅ መኾኑን አስገንዝበዋል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ግብርና ቢሮ ግብርና መምሪያ ኀላፊ አበበ መኮንን በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በደን ልማት ለመኖ እና ሁለገብ አገልግሎት የሚውሉ ችግኞች ለተከላ ስለመዘጋጀታቸው ተናግረዋል። በተያዘው ክረምት ”በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ መልዕክት ከሐምሌ አንድ ጀምሮ በሁሉም ወረዳዎች የችግኝ ተከላ ሥራ እንደሚከናወን ገልጸዋል። ለዚህም የቦታ ልየታ እና የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleሰላምን የዕውነት መኖር እና መገለጫ ማድረግ ይገባል።
Next articleችግኞች ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጡ መንከባከብ እና መከታተል ይገባል።