ሰላምን የዕውነት መኖር እና መገለጫ ማድረግ ይገባል።

10

ደሴ፡ ሰኔ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ከዩኤንዲፒ የሰላም ድጋፍ ተቋም ጋር በመተባበር በክልሉ ካሉ ዞኖች እና ወረዳዎች ከተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የወጣቶች፣ የሴቶች፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የማኅበረሰብ አቀፍ የግጭት አፈታት የምክክር መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ አካሂዷል። በመድረኩ አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡት ወይዘሮ መሠረት አያሌው ሰላምን ለማምጣት እና ለመጠበቅ ሴቶች ድርሻቸው ከፍተኛ መኾኑን ጠቅሰዋል። ሴቶች ቤተሰቦቻቸውን በመምከር ወደ ትክክለኛው መንገድ ማምጣት እንደሚገባቸው ነው የተናገሩት።

የሀገር ሽማግሌው አቶ ደምስ አበበ በበኩላቸው የሀገር ሽማግሌዎች እንደ ጥንቱ ትክክለኛ እና ቀጥተኛ በኾነ መንገድ ግጭቶችን መፍታት እና አፈንግጠው የወጡ ኅይሎችን ወደ ሰላማዊ መንገድ ማምጣት አለብን ብለዋል። በውይይቱ ተሳታፊ ከኾኑት የሃይማኖት አባቶች ሊቀ ትጉሃን ሰሎሞን አሰፋ እና ሼህ መሐመድ አብራር እንደተናገሩት ሰላም በዚች ምድር ላይ ውዱ ነገር መኾኑን አስገንዝበዋል። ሰላም የሁሉም ነገር ቀዳሚ ነው፣ ሁሉም መልካም ነገር የሚመጣው እና ትርፍ የሚገኘው ከሰላም ነው ብለዋል። የሃይማኖት አባቶቹ “ስለ ሰላም የምናስተምረውን ያህል በዕውነትም ልንኖረው ይገባል” ነው ያሉት። ሕዝቡ የሚፈልገው የጥይት ጩኸትን ሳይኾን ሰላም እና ልማትን መኾኑንም አስገንዝበዋል።

የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ አማካሪ ኮሎኔል ባምላኩ ዓባይ የክልሉ ሰላም በመናጋቱ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መከሰታቸውን አንስተዋል። የሕዝብ ጥያቄ አለኝ ያለ አካል የራሱን ሕዝብ እያንገላታ፣ እየዘረፈ፣ እየገደለ ልጆቹን ከትምህርት እየከለከለ እና በልማት ወደ ኋላ እያስቀረ መኾኑን ሁሉም ሊገነዘብ እና ሊታገለው ይገባልም ብለዋል።

የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ሁሉም ያመነባቸው እና መንግሥትም የያዛቸው ናቸው ያሉት አማካሪው በጠብመንጃ አፈሙዝ ሳይኾን በውይይት እና ድርድር የሚፈቱ መኾናቸውንም ጠቅሰዋል። የተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ የክልሉን ሀብት ከማውደም እና ወደ ኋላ ከማስቀረት ባለፈ የሚያስገኘው ውጤት እንደሌለም አመላክተዋል። ለሰላሙ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

ዘጋቢ ፡- መሐመድ በቀለ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለማቃለል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ትልቅ ድርሻ እያበረከተ ነው።
Next articleበምሥራቅ ጎጃም ዞን ከ228 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል።