
ደብረብርሃን፡ ሰኔ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት የበጋ በጎ ፈቃድ መዝጊያ እና 2018 በጀት ዓመት የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል። የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ አውራሪስ አረጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የእርስ በእርስ የመደጋገፍ እሴትን እያጎለበተ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በበጋ በጎፈቃድ አገልግሎት በ14 ዘርፎች አገልግሎት እየተሰጠ መቆየቱንም አብራርተዋል።
በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 92 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍል ለማሳተፍ መታቀዱንም አንስተዋል። ከዚህ ውስጥ ከ60 ሺህ በላይ የሚኾኑት ወጣቶች መኾናቸውም ተገልጿል ። 82 ሚሊዮን ብር የሚገመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት መታቀዱንም አስገንዝበዋል።
በክረምቱ ወራት በ18 ዘርፎች 165 ቤቶችን ለማደስ እና 252 ቤቶችን በአዲስ ለመሥራት ጥረት እየተደረገ መኾኑንም አብራርተዋል። 2ሺህ 500 ዩኒት ደም ለመሠብሠብ መታቀዱንም ገልጸዋል።
የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በጎነት ለሌሎች ገንዘብን፣ ጉልበትን እና ሀሳብን በማዋጣት የችግረኞችን እንባ ማበስ መኾኑን ጠቁመዋል። በከተማ አሥተዳደሩ ያሉ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቃለል በጎ ፈቃድ አገልግሎት ትልቅ ድርሻ እያበረከተ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
ዘጋቢ፦ ገንዘብ ታደሰ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን