
አዲስ አበባ፡ ሰኔ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 3ኛው የአፍሪካ ሥራ ፈጠራ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። ፎረሙን የከፈቱት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ኢንዱስትሪዎች እና የንግድ ተቋማት በተስፋፉ ቁጥር የሚፈጠረው የሥራ ዕድልም እንደሚጨምር ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለበርካቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚ በማድረግ ላይ እንደምትገኝም ገልጸዋል።
ፎረሙ እንደሌሎች መደበኛ ሥብሠባዎች የሚታይ ሳይኾን እንደአህጉር በጋራ ለመሥራት ትልቅ መሠረት የሚጣልበት እና ከቃል ወደተግባር በመሸጋገር ለወጣቶች የሚገባቸውን የወደፊት ሕይወት የሚያገኙበት ሊኾን ይገባል ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው እና በ10 ዓመት ዕቅዱ በየዓመቱ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ገልጸዋል። ሚኒስትሯ የሥራ ፈጠራ ምህዳሩን ለማስፋት በአህጉሪቱ እና በዓለምአቀፍ ደረጃ በትብብር እየተሠራ ነው ብለዋል።
በአህጉሪቱ ያለውን ተፈጥሮአዊ እና ሰው ሠራሽ አቅም በአግባቡ ተጠቅሞ ለመሥራት ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር በትብብር ለመሥራት እና ተሞክሮ ለመቅሰም ቁርጠኛ መኾኗንም ገልጸዋል። የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሐመድ አሊ የሱፍ ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በግብርናው ዘርፍ እየሠራች ያለውን ውጤታማ ሥራ አድንቀዋል፡፡
በአህጉሪቷ ግብርና በስፋት የሚሠራበት ዘርፍ እንደመኾኑ ከግሉ ዘርፍ ጋር በመቀናጀት የሥራ ዕድል በመፍጠር ለድህነት ቅነሳ ማዋል ይገባልም ብለዋል፡፡ ፎረሙ ለተከታታይ ሦሥት ቀናት ይቀጥላል። በፎረሙ ላይ የተለያዩ ሀገራት ሚኒስትሮች፣ የግሉ ዘርፍ ተወካዮች እና የተለያዩ አካላት እየተሳተፉበት ነው። በፎረሙ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ከደቡብ ሱዳን እና ከኤኢ ትሬድ ግሩፕ ጋር የተለያዩ ስምምነቶችን ያደርጋል ተብሎም ይጠበቃል፡፡
ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን