የአማራ ልማት ማኅበር የተጀመረው ራስን በራስ የማልማት አቅም ይበልጥ እንዲጠናከር ኢትዮጵያውያን ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቀረበ።

10

ባሕርዳር፡ ሰኔ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአልማ ሳምንትን ከሐምሌ 1/2017 ዓ.ም እስከ ሐምሌ15/2017 ዓ.ም እንደሚከበር ተገልጿል። የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ባለፉት 32 ዓመታት ከአባላት እና ከአጋር አካላት በተገኘ የልማት ሀብት የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ማኅበሩ አሁን ላይ ከ4 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ መደበኛ አባላት ያሉት ማኅበር ነው።

ማኅበሩ ከ2012 ዓ.ም እስከ 2016 ዓ.ም ባሉት አምስት ዓመታት ብቻ ከ7 ቢሊዮን 877 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት በማሠባሠብ የተለያዩ ሥራዎችን ማከናወኑን የአልማ ስትራቴጅ እና ኢኖቬሽን ምክትል ዋና ሥራ አሥፈጻሚ አበረ መኩሪያ አብራርተዋል።
ያለፉት አምስት ዓመታት የአልማ የሀብት ማሠባሠብ ምጣኔ በሦሥት እጥፍ ማደጉንም ነው የገለጹት።

ማኅበሩ ከ2012 ዓ.ም እስከ 2016 ዓ.ም ባሉት ዓመታት ከአጋር አካላት (መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች) ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ መሠብሠብ ችሏል። በዚህም ከ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል። የዲያስፖራው ማኅበረሰብ ደግሞ በገንዘብ፣ በፕሮጀክት እና በአይነት ከ185 ሚሊዮን በላይ ብር የሚገመት ሀብት ማበርከቱን ነው የገለጹት።

በተሠበሠበው ሀብት 2 ሺህ 952 የመማሪያ ከፍሎች እና 114 ጤና ጣቢያዎች፣ ጤና ኬላዎች እና የነፍሰጡር ማቆያዎች ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል ነው ያሉት። በ68 የቴክኒክ እና የሙያ ኮሌጆች የወርክ ሾፕ እና የሸድ ግንባታዎችን በማከናወን የክልሉን ሕዝብ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። ከዚህም ባለፈ 194 የእንስሳት ጤና ኬላ፣ አምቡላንስ እና የመሳሰሉትን የተለያዩ ፕሮጀከቶች ለአገልግሎት ማብቃት መቻሉንም ገልጸዋል። በጎርፍ፣ በመሬት መንሸራተት እና በአንበጣ ጉዳት ለደረሰባቸው 313 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።

ማኅበሩ ከሐምሌ 1/2017 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 15/2017 ዓ.ም የአልማ ሳምንትን ያከብራል።
በዚህም ለአልማ እሮጣለሁ፣ ማኅበሩ በሠራቸው ተቋማት የችግኝ ተከላ፣ የደም ልገሳ፣ የተገነቡ የልማት ሥራዎች ምረቃ፣ ጉብኝት እና የአልማ ጉባኤ ይካሄዳል።
አልማ የጀመረውን ራስን በራስ የማልማት አቅም ይበልጥ እንዲጠናከር በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበደሴ ከተማ በዓመቱ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ114 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ለማዳን ታቅዷል።
Next article“ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከአካባቢ ልማት ባሻገር በርካቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ ችላለች” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ