
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 25/2012 ዓ.ም (አብመድ) ለኢትዮጵያ የፊደል ገበታ በመቅረፅ ብርሃን የሆኑት ቀኝ አዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ በ1895 ዓ.ም ነበር የተወለዱት፡፡ ለቤተሰባቸው ስምንተኛ ልጅ ናቸው፡፡ አርበኛ፣ ደራሲ እና አሳታሚ ቀኝ አዝማች ተሰፋ ገብረሥላሴ፤ በልጅነታቸው ነበር ከአባታቸው እግር ስር ቁጭ ብለው ፊደል መማር የጀመሩት፡፡ ከዚያም በደብረ ታቦር ዙሪያ ከፍተኛ ሊቅ ተብለው ከተመሰከረላቸው ከመምህር ዘካሪያስ እንድሪያስ ዘንድ የንባብ ትምህርት ተከታትለዋል፡፡
በትምህርት አቀባበላቸውም የቀለም ቀንድ የሚባሉ ነበሩ፡፡ በውጤቱም በወርቀ ዘቦ የተንቆጠቆጠ ካባ እና ቀሚስ ተበርክቶላቸው ነበር፡፡ ከጎንደር ከፍተኛ ዕውቀትን ይዞ ሸዋ ለገባው ወጣት በወቅቱ ንጉሥ በአማካሪነት ሊሾሙት ቢፈለግም ምርጫው ሌሎቹን ማስተማር ስለነበር ሹመቱን ሳይቀበል ቀረ፡፡
አባታቸው መምህር ገብረሥላሴ ቢልልኝ በቡልጋ አክርሚት ሲኖሩ ቤተክርስቲያንን በማገልገል እና በሌላ በኩል ደግሞ ቀለም እየበጠበጡ ብራና እየፋቁ ለቀዬው ሕዝብ መጽሐፍ እያዘጋጁ ሲያድሉ እንደነበርም ከግል ታሪካቸው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ብላቴናውም ከዚህ በመነሳት የጽሑፍ ፍቅር እንዳደረበትም ታሪክ ያስረዳል፡፡
ተስፋ ለጽሕፈት ሥራቸው የበለጠ መቃናት ወደ አዲስ አበባ ያቀናሉ፡፡ በዚያን ዘመን አዲስ አበባ በትንንሽ የጎጆ ቤቶች፣ በዱር እና በቤት እንስሳት ጭር የተሞላች ነበረች፡፡ በተለይም ዓፄ ምኒልክም ከአንኮበር ወደ አዲስ አባባ ከመምጣቸው ጋር ተያይዞ ከአንኮበር ቤተ መንግሥት በተወረሱ ስሞች ትጠራ ነበረ፡፡ ብላቴናውም በፒያሳ፣ አራዳ፣ ፊት በር፣ አራት ኪሎ፣ አምስት ኪሎ እና ስድስት ኪሎ አካባቢዎች እየተዘዋወረ መኖር ጀምሯል፡፡ ይህን ሁሉ ሲያከናውን የነበረው ደግሞ አዲስ አበባ ይኖር ከነበረው ከታላቅ ወንድሙ ጋር እንደነበር ወሰን ደበበ ማንደፍሮ “ዘመን ተሻጋሪ ባለ-ውለታ” በሚለው መጽሐፉ አትቷል፡፡
ከወንድሙ ቤት ሲኖር ደግሞ ያለ ሥራ መቀመጥ አልፈለገም፤ ይልቁንም 75 ሳንቲም ከወንድሙ ተበደረ፤ ከጅቡቲ በባቡር የሚመጣውን ሽቶ በመግዛት እሪ በከንቱ በሚባል አካባቢ ለሚገኙ መጠጥ ቤቶች እና በዚያው አካባቢ ለሚገኙ ሁሉ ሲያከፋፍል ቆየ፡፡ በዚህም ዳጎስ ያለ ብር ማገኘት እንደቻለ ታሪኩ ያስረዳል፡፡
“ሥራ የሚጠላ በዚህ ምድር መኖርን የጠላ ብቻ ነው፤ ‘ሙያ፣ ክብር፣ ጥላቻ፣ ንቀት’ በማለት መመጻደቅ በዚህች ድሀ ሀገር በድሀ ሕዝብና ሀገር ላይ ማላገጥ ነው፤ የሰው ልጅ ለሚሠራው ሥራ ክብር ሲሰጥ ብቻ ነው ለኅሊናው እርካታ የሚያገኘው” የሚል ሐሳብ ያራምዳል፡፡ በተግባርም ትንሹ ተስፋ ከሽቶ ንግድ ወደ መጻሕፍት ንግድ ገባ፡፡ በተለይም በዓፄ ቴዎድሮስ የንግሥና ዘመን መጨረሻ ለወንጌል አገልግሎት ወደ ኢትዮጵያ ከገቡት ሚሲዮናዊ ሚስተር ዴቪድ ጋር በመሆን መንፈሳዊ መጻሕፍት ተዘዋውሮ በመሸጥም ስኬታማ ነበር፤ ወጣቱ፡፡
በዘመኑ እንደ ዛሬው መጽሕፍ የሚገዛ ሰው ባለመኖሩ ደግሞ ለመኳንንት እና ሹማምንት ልጆች እየዞረ ያስረክብ ነበር፡፡ ማንበብና መጻፍ ለማይችሉት ደግሞ እሱ ያነብላቸው እንደነበርም ይነገራል፡፡ በዚህ ጊዜም አንዳንድ ሽማግሌዎች “አንተንም ጨምረን እንግዛህ፤ የሚያነብልን የለም” ይሉት ነበር ይባላል፡፡ ብዙው ሰው ማንበብ እና መጻፍ የማይችል መሆኑ ደግሞ ተስፋን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በቀላል ዋጋ ገዝቶ ማንበብ የሚያስችል የፊደል ገበታ ለመፍጠር አነሳሳው፡፡ ያሰበውንም ለማሳካት ቀለም በመበጥበጥ፣ በብራና ላይ ፊደል በመቅረጽ፣ ኢትዮጵያ የራሷ ዘመናዊ የፊደል ገበታ እንዲኖራት አድርጓል፡፡ እናም ስማቸው በሁሉም ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ታትሞ እንዲኖር ሆኗል፡፡
የአብመድ የጋዜጠኞች ቡድን ደግሞ የእርሳቸው ሃውልት በተሠራበት የበረኸት ወረዳ አክርሚት ቀበሌ ተገኝቷል፤ ወጣቶች የእርሳቸውን አርዓያነት ለመከተል እና ሥራቸውን ለማስታወስ እየሠሩ ያሉትን ሥራም ተመልክቷል፡፡ በበረኸት ወረዳ አክርሚት ቀበሌ ነዋሪው ወጣት ደረጀ ተስፋዬ “ተስፋ ገበረሥላሴ ለሁሉም ኢትዮጵያ ብርሃን ናቸው፤ እኛም የእርሳቸውን ፈለግ ተክትለን መልካም ሥራ እየሠራን ነው” ብሏል፡፡ ወጣቶቹ አረጋውያንን መርዳት እና መሰል የበጎ አድራጎት ሥራ በመሥራት ወጣቱ በመልካም ስብዕና እንዲታነጽ እየተደረገ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ የዛሬው ትውልድም እንደ እርሳቸው ለኢትዮጵያ ብርሃን ለመሆን መሥራት አለበትም ብሏል፡፡
ሌላኛው ወጣት ዳንኤል ገሰሰ ትውልዱም የእርሳቸውን ታሪክ ወደ ኋላ እያሰበ የራሱን ታሪክ መሥራት እንዳለበት ተናግሯል፡፡ በወረዳቸው ወጣቶች በተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎች እንደሚሳተፉ እና በትምህርትም ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግሯል፡፡
የበረኸት ወረዳ የባህል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ብርቄ ሀብተሥላሴ ቀኝ አዝማች ተስፋ ገብረሥላሴን “የኢትዮጵያ ሥነ ትምህርት ታሪክ እንዲያድግና የሕትመት ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ ፈር ቀዳጅ ኢትዮጵያዊ አርበኛ ናቸው” ሲሉ ገልጸዋቸዋል፡፡
ለመታሰቢያቸውም በወረዳው በ5 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት በግንባታ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፤ ይህ ደግሞ እርሳቸው ለዕውቀት የነበራቸውን ፅኑ እምነት ለትውልዱ ለማስተላለፍ እንደሚያግዝ ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እርሳቸው በኢትዮጵያ ትልቅ አሻራ ያላቸው በመሆኑ ትውልዱ የእርሳቸውን ፈለግ ሊከተል እንደሚገባ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
