በደሴ ከተማ በዓመቱ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ114 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ለማዳን ታቅዷል።

13

ደሴ፡ ሰኔ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደሴ ከተማ አሥተዳደር “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ መልዕክት የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የማስጀመሪያ የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል። አሚኮ ያነጋገራቸው በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች የበጎ ፍቃድ ሥራን በራስ ተነሳሽነት እና በራስ አቅም በተለያዩ ዘርፎች ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል። ለዚህም ክፍያው የሕሊና እርካታ ነው ያሉት ወጣቶቹ በዘንድሮው የበጎ ፈቃድ ተግባር ከአምናው በተሻለ መልኩ ተግባራትን ለመፈፀም ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

የደሴ ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ሰይድ አራጋው በጎ ፈቃድ ዘርፈ ብዙ እና ሕዝብን ከሕዝብ የሚያስተሳስር ተግባር መኾኑን አንስተዋል። የዘንድሮው የክረምት በጎ ፍቃድ በመንግሥት ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸው በደሴ ከተማ በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ 17 የተለያዩ የበጎ ፈቃድ ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል። በዚህ ዓመት የክረምት በጎ ፍቃድ ከ140 ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ክፍልን ተጠቃሚ በማድረግ ከ114 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ለማዳን መታቀዱን ገልጸዋል። የደሴ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ሺመልስ ጌታቸው የዚህ ዓመትን የክረምት በጎ ፍቃድ ከአምናው በተሻለ መልኩ ለመሥራት መታቀዱን ጠቁመዋል።

በአካባቢ ጥበቃ፣ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር፣ የአረጋውያንን ቤት የማደስ እና የመጠገን፣ የደም ልገሳ፣ የማዕድ ማጋራት እና የተማሪዎች የትምህርት መሳሪያ ቁሳቁስ እና የአልባሳት ድጋፍ በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት ናቸውም ብለዋል። የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጅ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ጥላሁን ሺመልስ የበጎ ተግባር ለወሎ ሕዝብ የረጅም ግዜ እሴት ኾኖ መዝለቁን አንስተዋል። ሰው ተኮር ሥራ መሥራት ማለት በሌላ ቋንቋ ለሰዎች በጎ ነገር ማድረግ ነውም ብለዋል። በክረምቱ ለመሥራት ከታቀዱ 17 የበጎ ሥራ ተግባራት ባለፈ ሁሉም ሊከውነው የሚገባው የአካባቢን ሰላም መጠበቅ ነው ብለዋል። በዚህም ሰላምን አንዱ የበጎነት መገለጫ አድርጎ መውሰድ እና መተግበር ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

ዘጋቢ:- መስዑድ ጀማል

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleሰላምን ለማጽናት ቁርጠኞች መኾን አለባችሁ።
Next articleየአማራ ልማት ማኅበር የተጀመረው ራስን በራስ የማልማት አቅም ይበልጥ እንዲጠናከር ኢትዮጵያውያን ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቀረበ።