ሰላምን ለማጽናት ቁርጠኞች መኾን አለባችሁ።

4

ወልድያ: ሰኔ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ ሰላምን ለማረጋገጥ የሠለጠኑ ሚሊሻዎች ተመርቀዋል። በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥዳዳሪ አራጌ ይመር ሠልጣኞቹ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመኾን ቀጣናቸውን እና ሕዝባቸውን እንዲጠብቁ አሳስበዋል።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ምሥራቅ ዕዝ 801ኛ ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ዘውዱ ሰጥአርጌ በወቅታዊ ችግሮች ላይ ወጥ አረዳድ ቢፈጠር ኖሮ ችግሩ አይባባስም ነበር ብለዋል። ሠልጣኞች እርስ በእርስ መተማመንና መደጋገፍ እንዳለባቸው ገልጸዋል። ጓዳዊ አንድነትና እርስ በእርስ መተማመን ሰላምን ለማጽናት ለሚደረገው ሥራ ቁልፍ ነው ብለዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት በአስፈላጊው ዘርፍ ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ደንና አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ኀላፊ ኮማንደር መንገሻ አውራሪስ ሠልጣኞች ከወረዳቸው አልፈው የክልሉን ሰላም ለማጽናት ቁርጠኞች እንዲሆኑ ጠይቀዋል። የክልሉ መንግሥትም ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት። የሀብሩ ወረዳ ዋና አሥተዳደሪ ሁሴን ሙሐመድ ተመራቂዎቹ ከየቀበሌው የተውጣጡ የሚሊሻ አባላት መሆናቸውን ነው ያስረዱት። የአካባቢያቸውን ሰላም ለመጠበቅ ቀናኢ የኾኑ ባለምግባር የሕዝብ ልጆች መኾናቸውንም ተናግረዋል።

በምረቃው ላይ የተገኙት የሀገር ሽማግሌ እና የሃይማኖት አባት ሼህ ሀሰን ከረሙ እንዳሉት እንደ ሕዝብ ወጥ ሥነልቦና ከያዝን አጥፊዎች መክረን ልንመልሳቸው የምንችላቸው ልጆቻችን ናቸው ነው ያሉት። “ሁላችንም ልጆቻችንን ተው ማለት አለብን” ያሉት ሼህ ሀሰን ከረሙ ይህንን ጥሪ በማይቀበሉት ላይ ሕግ የማሥከበር ሥራ መከናወን አለበት ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከሰላም ግንባታው ጎን ለጎን የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት አየሠራ መኾኑን የምዕራብ ጎጃም ዞን አስታወቀ።
Next articleበደሴ ከተማ በዓመቱ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ114 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ለማዳን ታቅዷል።