
ፍኖተሰላም፡ ሰኔ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጸጥታ ችግሩ በምዕራብ ጎጃም ዞን ኅብረተሰቡ ከሁለንተናዊ እንቅስቃሴው እዲገታ በማድረግ ለተለያዩ ቀውሶች እንደዳረገው ተገልጿል።
ይህንን የጸጥታ ችግር የሚቃወም እና ሰላምን የሚሻ በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች የኅብረተሰብ ድምጾች ተስተጋብተዋል።
ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህ በተለያዩ ወረዳዎች ሕዝቡ የድጋፍ ሰልፍ በማካሄድ ሰላም እንዲመጣ እና ሕግ እንዲከበር በአደባባይ ጠይቋል ብለዋል።
እየደረሰ ያለውን ሁለንተናዊ ቀውስ ተረድተው የታጠቁ ኀይሎች የሰላምን መንገድ እንዲከተሉም ኅብረተሰቡ ጠይቋል ነው ያሉት።
ኅብረተሰቡ ለበርካታ ዓመታት ተጠይቀው ምላሽ አግኝተው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ማንሳቱንም ገልጸዋል።
መንግሥት አሁንም ቢኾን ለሰላም ቅድሚያ እንደሚሰጥ ያነሱት አሥተዳዳሪው ከሰላም ግንባታው ጎን ለጎን የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት አየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
በዞኑ ለአርሶአደሮች የግብርና ሥራቸውን የሚያሳልጡ በዚህ ዓመት ብቻ የተሠሩ 14 ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት መኾናቸውን ገልጸዋል።
በርካታ የታጠቁ ኀይሎች የሰም አማራጩን እየተከተሉ መኾናቸውን የገለጹት ዋና አሥተዳዳሪው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲኾኑም ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ መኾኑን አንስተዋል።
የጸጥታ ችግሩ በፌዴራል መንግሥት የሚገነቡ ግዙፍ ስምንት የመብራት ኀይል ዝርጋታ እና የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክቶች በሚፈለገው ልክ እንዳይከናወኑ እያደረጋቸው እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ኅብረተሰቡ የሰላም ባለቤት በመኾን ሰላሙ ዘላቂ እንዲኾን ሁለንተናዊ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን