” የነገዋ አፍሪካ የምትገነባው በጋራ ጥረታችን ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

8

ባሕርዳር: ሰኔ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ሦስተኛውን የአፍሪካ ሥራ ዕድል ፈጠራ ጉባኤን ዛሬ አስጀምረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የነገዋ አፍሪካ የምትገነባው በጋራ ጥረታችን ነው።ሦስተኛውን የአፍሪካ ሥራ ዕድል ፈጠራ ጉባኤ ዛሬ በውቧ አዲስ አበባ ማስተናገድ ጀምረናል ብለዋል።

አፍሪካ የወጣቶች፣ የእምቅ ተፈጥሮ ሀብት እና የመለወጥ ሕልም ያላት አህጉር ናት ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወጣቶቻችን ጥንካሬዎቻችን፣ የወደፊት ተስፋዎቻችን እና የአህጉራችን የዕድገት አቅሞች ናቸው ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ለዚህ ፓን አፍሪካዊ ተልዕኮ በቁርጠኝነት እየሠራች ነው፣ ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራን ዋነኛ የትኩረት ማዕከል አድርጋ እየሠራች ትገኛለች ብለዋል።

በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የአስር ዓመታት የልማት እቅዳችን ወጣቶችን ጨምሮ ብቁ የሰው ኃይል እያፈራን፣ የታዳሽ ኃይል ልማትን እያሰፋን፣ ግብርናን እያዘመንን፣ ኢንዱስትሪዎችን እያሳደግን፣ ዲጂታል ኢኮኖሚን እየገነባን፣ ለዓየር ንብረት ለውጥ የማይበገር፣ አካታች እና የወደፊት ሁኔታን ያገናዘበ ጠንካራ ሀገራዊ አቅምም እየገነባን ነው።

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 40 ቢሊዮን ችግኝ ከመትከል ባለፈ ለበርካታ ወጣቶች፣ አርሶ አደሮች እና ሴቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ለብዙዎች የተስፋ ብርሃንን ፈንጥቀናል ነው ያሉት።

የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ ጉባኤ የክህሎት ልማት እና የጋራ ብልጽግና ፓን አፍሪካዊ ራዕዮቻችንን ለማሳካት፣ ከዕቅድ ባለፈ የተግባር ጉዟችንን የምናጠናክርበት ነው።

የተሻለች አፍሪካን ለመገንባት በተስፋ፣ በቁርጠኝነት እና በአንድነትን እንድንነሳ ጥሪዬን አቀርባለሁ ብለዋል በመልዕክታቸው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበእንጅባራ ከተማ በ575 ሚሊዮን ብር በኾነ ወጭ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ እና ማጣሪያ ሊገነባ ነው።
Next articleከሰላም ግንባታው ጎን ለጎን የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት አየሠራ መኾኑን የምዕራብ ጎጃም ዞን አስታወቀ።