በእንጅባራ ከተማ በ575 ሚሊዮን ብር በኾነ ወጭ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ እና ማጣሪያ ሊገነባ ነው።

6

እንጅባራ: ሰኔ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ፕሮጀክቱ ከጣሊያን የልማት አጋር ድርጅት በተገኘ በ575 ሚሊዮን ብር የረጅም ጊዜ ብድር የሚገነባ ነው ተብሏል።

ፕሮጀክቱ ከፍሳሽ ቆሻሻ ማጠራቀሚያና ማጣሪያ ፕላንት በተጨማሪ የመፀዳጃ ቤቶች ግንባታ እና የፍሳሽ ቆሻሻ መምጠጫ ተሽከርካሪ ግዢን ያካተተ ነው።

ፕሮጀክቱ ሰርጃ ኮንስትራክሽንና ጠቅላላ ንግድ ኀላፊነቱ የተወሰ የግል ማኅበር ከባይጌታ ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጋር በጣምራ እንደሚገባ ተገልጿል። በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ውል ተይዟል።

የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ የኔዓለም ዋሴ ፕሮጀክቱ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ ሁሉን አቀፍ ዘመናዊ የሳኒቴሽን መሠረተ ልማት በመገንባት ዘላቂነት ያለው አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መኾኑን ተናግረዋል። ለፕሮጀክት ግንባታ ከ3ኛ ወገን ነፃ የኾነ 4 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ርክክብ መፈጸሙንም ገልጸዋል።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው የብዙ ከተሞች የውበታቸው ሚስጥር ከተሞች በደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አያያዝ ላይ የወሰዱት ቁርጠኝ እርምጃ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ አሁን ላይ በከተማዋ የሚስተዋለውን ደካማ የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ለማዘመንና መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል መኾኑን ገልጸዋል ።

ልማት የሰከነ ሰላምን ይፈልጋል ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ኅብረተሰቡ ለሰላም ያለውን አጋርነት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የከተማው ነዋሪዎችም ፕሮጀክቱ ለሰላም የከፈልነው ዋጋ ውጤት ነው ብለዋል። ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሰኔ 30፤ ድሮ እና ዘንድሮ
Next article” የነገዋ አፍሪካ የምትገነባው በጋራ ጥረታችን ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ