
ባሕርዳር፡ ሰኔ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰኔ ወር ለአርሶ እደሮች፣ ለመንግሥት መስሪያ ቤት ሠራተኞች እና ለተማሪዎች እንደ ብርቅየዋ የመስቀል ወፍ ተናፋቂ ናት ቢባል ማጋነን አይኾንም።
የሰኔ ወር በተለይ ጎበዝ እና ደካማ ተማሪዎችን አንቀርቅባ የምትለይ ወንፊት በመኾኗ ትዝታዋ የትምህርት ቤትን ደጅ በረገጠ ሰው ህሊና እና ቅን ልቦና ውስጥ ሁሌም ትውስታዋ ከፍ ያለ ነው።
እውነት እላችኋለሁ! እኔ እስከ ሦሥተኛ ክፍል ድረስ ስማር በአንድ ዓመት ውስጥ ስንት ወራት እንዳሉ እንኳን አላውቅም ነበር።
የሰኔን ወር ያወቅሁት ሰኔ 30 ላይ ከክፍል ወደ ክፍል ያልተዘዋወሩ ተማሪዎች አንገታቸውን ደፍተው ሲቆዝሙ፣ ሲያለቅሱ እና ያዙኝ ልቀቁኝ ሲሉ “ለምን?” ብዬ በመጠየቄ ነው። መስከረም፣ ጥቅምት፣ ኅዳር፣ ታኅሳስ…እያልሁ በተማሪዎች ዘንድ እንደ መስቀል ወፍ ከምትናፈቀው ሰኔ 30 ላይ የደረስኩት።
በቀደመው ዘመን በአስኳላ ተማሪ ዘንድ የሰኔ 30 ትዝታ እና ትውስታ ሕልቆ መሳፍርት የለውም።
” ያረሰማ ጎበዝ እርፍ የነቀነቀ፣
ወፍጮው እንዳጓራ መስከረም ዘለቀ”
እንደሚባልለት ትጉህ ገበሬ፤ ዓመቱን ሙሉ ያጠና ተማሪ በሰኔ 30 ጠግቦ እንደጠባ እምቦሳ ሜዳ ሙሉ ይቦርቃል።
ይህኔ ፦
“ጠንክሮ ያጠና ጠይቆ ያወቀ፣ ሰነፎች ሲያለቅሱ እሱ ተሳለቀ” እየተባለ መወደሱን አስታውሳለሁ። ትዝታ አያረጅ አይደል!
በአንጻሩ ጊዜያቸውን በዋዛ ፈዛዛ አሳልፈው የዓመቱ የፈተና ውጤት ተደምሮ እና ተካፍሎ ስኔ 30 ላይ ወደ ቀጣዩ ክፍል መዛወር ተስኗቸው የሚቆዝሙ ተማሪዎች ቁጥር ቀላል አይደለም።
“አይ ሰኔ 30!
የተማሪ አበሳ!
መቼም አትረሳ!”
ጥቂት የማይባሉ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ታዛ ተከልለው ያዝናሉ።
ታዲያ እኒያ የቀለም ቀንዶቹ ደካማ ተማሪዎችን እንዲህ በማለት ይሳለቁባቸው እንደነበር ትዝይ ይለኛል።
“ሰኔ ሰላሳ፣
የለውም ካሳ።”
ሰኔ 30 ላይ የሚሰነዘሩ ትረባዎች አቧራ አስነስተው ከንፈር ያሳብጣሉ።
የተማሪውን ከንፈር ማበጥ ያዬ ቆቅ እና ንብ የኾነው ተማሪ፦
አንድ ኪሎ ሥጋ አከለ ከንፈሩ፣
ጠንክሮ አይማርም ደግሞ አለማፈሩ።
ተማሪው በትረባው እና ብሽሽቁ ዐይኑ ቅል አክሎ በርበሬ ቢመስልም “ቆይ አገኝሃለሁ” ብሎ ከመዛት ባሻገር ቡጢ ግን በጭራሽ አይሰነዝርም። ድንጋይ መወርወር አይሞከርም። ጠብ የሚጭር ተማሪ በፍጹም አይታሰብም፤ በእኔ ጊዜ…።
ሌላው ሰኔ 30 ላይ ውጤቱ ዝቅ ብሎ ጥሩ ደረጃ ያልያዘ፣ ያልተሽለመ ወይም በጣም ዝቅተኛ ውጤት አስመዝግቦ ወደ ቀጣዩ ክፍል መሽጋገር ያልቻለ ተማሪ መምህራንን ውጤት ለማጭበርበር መከጀል፣ ማንጓጠጥ እና መገላመጥ በፍጹም አያስበውም፤ አያደርገውምም።
በአንጻሩ መምህሩ በአጠገቡ የሚያልፍ ከኾነ ከመቀመጫው ተነስቶ በክብር እና በትህትና እጅ ይነሳል እንጅ አቂሞ አይወርፍም። ዛሬ እንደ ድሮው ለመኾኑ እርግጠኛ አይደለሁም።
ለነገሩ ጊዜን ጥሩም መጥፎም የሚያደርገው ሰው አይደል!
ብልህ ተማሪዎች አንድም ከራሳቸው ስህተት አልያም ከጓደኞቻቸው ጉብዝና ይማራሉ እንዲሉ ያኔ በ”ሰኔ 30፣ የለውም ካሳ” የተፎገሩ ተማሪዎች ይባሱን ሳይሰንፉ ይልቁንም ፉገራውን እንደመስፈንጠሪያ መሳሪያ ይጠቀሙበታል።
በዚህ ዓይነትም ስንት እና ስንት ተማሪዎች በእልህ እና ቁጭት ተነሳስተው ጠንክረው በማማር የደረጃ ተማሪ በመኾን ለመሽለም መብቃታቸውን አስታውሳለሁ።
ጉብዝናቸውን አስቀጥለውም ዩኒቨርሲቲ በመግባት በምሕንድስና፣ በሕክምና፣ በሥነ ትምህርት፣ በምርምር እና በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ተስማርተው ዛሬ ላይ ለሀገር እና ሕዝባቸው ምሰሶ በመኾን ውለታ ከፋይ ኾነዋል። አቤት ደስ ማለታቸው…ትዝታ አያረጅ አይደል…
ሰኔ 30 አሁን ላይ በተለያዩ ምክንያቶች በትምህርት ቤቶች የነበረው ክብር እና ውዳሴ ትዝታውን አስታቅፎ ብቻ ቀርቷል ባይ ነኝ።
በተለይ በአማራ ክልል በመስከረም ወር ትምህርትን ጀምሮ በሰኔ ወር መቋጨት የሚታሰብ አይደለም። ምክንያቱ ደግሞ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በክልሉ የገጠመው የጸጥታ ችግር መማር ማስተማሩን በብርቱ ፈትኖታል፤ ጎድቶታልምና ነው።
ጊዜን ጥሩም መጥፎም የሚያደርገው ስው ነው ያለው ማን ነበር? እንደዚያ ነው …
የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንዲሉ አንዱ አልሚ ኾኖ ሲገነባ ሌላው አጥፊ ኾኖ ያፈርሳል። አልሚው ትምህርት ቤት እየገነባ ወገኖችን አስተምሮ ለቁም ነገር ለማብቃት ቀን እና ሌሊት ይታትራል።
ሀገር ተበድራ እና ተቸግራ የገዛችውን የልጆቿን የመማሪያ መጻሕፍት የጽንፈኝነት ባሕርይ የተጠናወተው ልጇ ያቃጥላል። በስንት ልፋት የተገነባን ትምህርት ቤት ያወድማል። ጠመኔ በእጃቸው ይዘው ነጭ ጋዎን የለበሱ መምህራንን ይገድላል። ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ ያደርጋል።
በአማራ ክልል በ2017 የትምህርት ዘመን መማር ከነበረባቸው ከ7 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ውስጥ ትምህርት ቤት የገቡት 3 ሚሊዮኖች ብቻ ናቸው።
4 ሚሊዮን ተማሪዎች መማርን እንደናፈቁ ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነው ከርመዋል። በመስከረም ትምህርት ጀምረው በሰኔ መቋጨት እየናፈቃቸው ትምህርት በዐይናቸው ሲዞር ባጅቷል። በሕዳር፣ የካቲት፣ ሚያዚያ ብቻ በመቼውም ወራት ትምህርት ጀምረው መቼውንም ለመጨረስ ቢሹም አልቻሉም። ያሳዝናል!
ከተለያዩ የታሪክ መዛግብት እንደምንረዳው በኢትዮጵያ ታሪክ የተነሱ የተለያዩ ዘውግን አንግበው በመንግሥት ላይ ብረት ያነሱ ኀይላት ትምህርትን የከለከሉበት ወቅት አልተመዘገበም። ኑሮም አያውቅም። ትምህርት ቤቶች በመስከረም ወር በሰላም ተከፍተው ሲያስተምሩ ከርመው በሰኔ ወር በሰላም ይዘጋሉ እንጂ። ዛሬ ግን እሱ ለአሁኑ ትውልድ አልተቻለም፤ ነገር ግን ነገ ሌላ ቀን ነው። በበርካታ ውጣ ውረድ ውስጥም ኾናችሁ የዚህን ዓመት ትምህርታችሁን ላጠናቀቃችሁ ሁሉ መልካም ሰኔ 30!
በሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
