ከ87 ሚሊዮን ብር ያላነሰ ወጭ ወጥቶም የነዋሪዎች ውኃ ጥም አልተፈታም፡፡

187

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 24/2012 ዓ.ም (አብመድ)

• ‘‘20 የማስተካከያ ሥራዎች ሳይመለሱ ባላወቅነው መንገድ ርክክቡን መፈጸማችን ተነገረን፡፡’’ የዋድላ ውኃ፣ መስኖ ኢነርጂ ጽሕፈት ቤት
• ‘‘ለማን እንዳስረከበ ሕዝቡም የወረዳ አስተዳደሩም ሳያውቅ ርክክብ መፈጸሙን መረጃ ደርሶናል፡፡’’ የዋድላ መቄት የውኃ ፕሮጀክት
• ‘‘አውሥኮድ በውሉ መሠረት ሁሉንም ሥራዎች በጥራት አከናውኖ በኅብረተሰቡ ይሁንታ አስረክቧል፡፡’’ አውሥኮድ
• ‘‘የጥራት ጉድለቶች መኖራቸውን ቢሮ ቢያውቅም የማሻሻያ ጥያቄዎችን መመለስ የሚያስችል በጀት የለንም፡፡’’ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጅ ቢሮ

በዋድላና መቄት ወረዳዎች 8 ቀበሌዎችን የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ ለማድረግ በአማራ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት (አውሥኮድ) በ87 ሚሊዮን ብር ወጭ በ2010 ዓ.ም ተገንብቷል፡፡ ፕሮጀክቱ ቢጠናቀቅም ከሁለት ዓመታት በላይ አስፈላጊውን አገልግሎት እየሰጠ ባለመሆኑ ነዋሪዎች ከፍተኛ ቅሬታ አላቸው፡፡

ከቅሬታ አቅራቢዎች መካከል የ017 ቀበሌ ነዋሪው አቶ ወርቁ ቢምረው አንዱ ናቸው፡፡ አቶ ወርቁ በቀበሌው ከሁለት ዓመታት በፊት ምንም ዓይነት የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚነት ባለመኖሩ የፕሮጀክቱ መጀመር ትልቅ ተስፋን ይዞ መጥቶ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ የምንጭ ውኃ ለመቅዳት በየቀኑ ከሁለት ሰዓታት በላይ እንደሚጓዙም ተናግረዋል፡፡ የዋድላ መቄት የውኃ ፕሮጀክት ሥራ መጀመሩን ተከትሎ ከውኃ ወለድ በሽታዎች ለመጠበቅ፣ ከእንግልት እና ከጉልበት ብክነት እንደሚድኑ ተስፋ ቢያደርጉም የፓንፕ መፈንዳት እና መቆራረጥ ምክንያት ግን ተስፋ ባደረጉት ፕሮጀክት መጠቀም እንዳልቻሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

ሌላዋ የ016 ቀበሌ ሮቢት ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ባንቻየሁ አቻሙ ደግሞ በከተማዋ ዛሬም ድረስ ፕሮጀክቱ አስፈላጊውን አገልግሎት ባለመስጠቱ ረጅም ርቀት ተጉዘው የምንጭ ውኃ ለመቅዳት መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡ በውኃ እጥረቱ ምክንያት ከምንጭ ውኃ ቦታዎች የሚፈጠሩ ግጭቶች ከፍተኛ ናቸው የሚሉት ወይዘሮ ባንቻየሁ የምንጭ ውኃ በጥራት ስለማይቀዳ በተደጋጋሚ ለውኃ ወለድ በሽታዎች ተጋላጭ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

የዋድላ ወረዳ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ቁምነገር ደሳለኝ ‘‘የውኃ ፕሮጀክቱ ተገቢውን አገልግሎት ባለመስጠቱ የነዋሪዎች እና የአስተዳደሩ የቅሬታ ምንጭ ሆኗል’’ ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ከሁለት ዓመታት በፊት ቢጠናቀቅም ከ20 በላይ ልዩ ልዩ ችግሮች እንዳሉ ወረዳው በተደጋጋሚ ለአውሥኮድና ውኃ ቢሮ ማስታወቁን አቶ ቁምነገር ተናግረዋል፡፡ አውሥኮድ ከቅሬታዎቹ አምስቱን ቢፈታም 87 ሚሊዮን ብር ወጭ የተደረገበት ፕሮጀክት ግን ‘‘የታለመለትን አገልግሎት እየሰጠ አይደለም’’ ነው ያሉት፡፡ አቶ ቁምነገር ‘‘የሕዝብ እና የመንግሥት ሀብት በመባከኑ ወረዳው ፕሮጀክቱን እንደማይረከበው ቢያስታውቅም፤ ባላወቅነው መንገድ ርክክቡን መፈጸማችን ተነገረን’’ ብለዋል፡፡

የዋድላ መቄት የውኃ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብተማሪያም አሊ ‘‘ፕሮጀክቱ ቀበሌዎችን አላደረሰም፡፡ መስጠት ከነበረበት አገልግሎት 50 በመቶ ብቻ ነው እያቆራረጠ የሚሠራው’’ ነው ያሉት፡፡ ሥራ አስኪያጁ የዋድላ መቄት ‘‘የውኃ ፕሮጀክት የጥራት እና ዲዛይን ችግር እንዳለበት ሪፖርት ቢደረግም የሠራው አካል ለማን እንዳስረከበ ሕዝቡም የወረዳ አስተዳደሩም ሳያውቅ ርክክብ መፈጸሙን መረጃ ደርሶናል’’ ብለዋል፡፡

የአማራ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ አቶ ብርሃኑ ዮሐንስ ግን ‘‘ሥራው ሳይጠናቀቅ በአውሥኮድ በኩልም ሆነ በሌላ አካል አማካኝነት ርክክብ እንዲፈጸም ጫና አላደረግንም፡፡ አውሥኮድ በውሉ መሠረት ሁሉንም ሥራዎች በጥራት አከናውኖ በኅብረተሰቡ ይሁንታ አስረክቧል’’ ብለዋል፡፡ አብመድ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ዛሬም የምንጭ ውኃ እንደሚቀዱ ተናግረዋል፤ ወረዳው ‘‘ያለዕውቅናችን ርክክብ ተፈጽሟል’’ የሚል ቅሬታ እንዳላቸው አብመድ ከመረጃ ምንጮቹ አግኝቷል፡፡

ወረዳው አውሥኮድ ከ20 የማስተካከያ ጥያቄዎች አምስቱን መልሷል ቢልም አቶ ብርሃኑ ግን ‘‘አውሥኮድ በውሉ መሠረት ሁሉንም ሥራዎች በጥራት ሠርቷል፤ የመጨረሻ ርክክብ ለማድረግም በወረዳው የቀረቡ ጉድለቶችን ጥገና በማድረግ እና በማስተካከል አስረክቧል’’ ነው ያሉት፡፡ የሚነሱ ቅሬታዎች ካሉ ወረዳውና የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ቢሮ አዲስ ውል አስይዘው ሊያሠሩት እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡

የክልሉ ውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ልማት ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አደም ወርቁ አውሥኮድ በጥራት ሠርቻለሁ ካለው ሐሳብ በተቃራኒ ‘‘የጥራት ጉድለቶች መኖራቸውን ቢሮ ቢያውቅም የማሻሻያ ጥያቄዎችን መመለስ የሚያስችል በጀት የለንም’’ ብለዋል፡፡ ክልሉ በበጀት እጥረት መመለስ ያልቻላቸውን የሕዝብ ቅሬታዎችና ጥያቄዎችን ‘‘ዞኑና የወረዳ መዋቅሩ ሊመልሷቸው ይገባል’’ በማለት ገፍተውታል፡፡

አቶ አደም ትልቁ ፈተናቸው ፕሮጀክቶች እንደተጠናቀቁ የሚረከብ አለመገኘት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ዋድላ መቄት የውኃ ፕሮጀክት ርክክብ ጫና ነበረው ለሚለው ሐሳብም ‘‘ርክክብ የተፈጸመው ፕሮጀክቱን በባለቤትነት ማስተዳደር እንዲቻል ከማሰብ እንጂ ሌላ ዓላማ ያለው ሰው የለም’’ ብለዋል፡፡ የፕሮጀክት ርክክቦች ላይ ‘‘ሁሉም ነገር ካልተስተካከለ አንረከብም’ የሚሉ ባለሙያዎች አሉ’’ ያሉት አቶ አደም መቼም ቢሆን ንጹሕ ፕሮጀክት ማስረከብ እንደማይቻልም ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ያለዘላቂ ተጠቃሚነት ከ87 ሚሊዮን ብር በላይ የሕዝብ እና የመንግሥት በጀት ወጭ ተደርጎበት ቆሟል፡፡ ሕዝቡ ዛሬም ከምንጭ ውኃ ከመቅዳት ልማዱ አልወጣም፤ የቅሬታ ምንጭ በመሆን ሌላ የቤት ሥራን ለመንግሥት እየተፈጠረም ነው፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ

Previous articleሩዋንዳ ገደቦችን የማላላት ውሳኔዋን ሻረች፡፡
Next articleየፊደል ገበታው አባት ጌታ ቀኝ አዝማች ተሰፋ ገብረሥላሴ