
ባሕርዳር: ሰኔ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሪዮ ዲ ጄኒሮ እየተካሄደ በሚገኘው 17ኛው የብሪክስ ጉባኤ የሰላም፣ የጸጥታ እና ዓለምአቀፍ አመራር መድረክ መክፈቻ ላይ ንግግር አድርገዋል።
በንግግራቸውም ስኬታማ ትብብርን ለማስቻል አፀፋዊ መተማመንን የሚያሳድጉ ዓለምአቀፍ ተቋማት የመኖርን አጣዳፊነት አንስተዋል።
ዓለምአቀፍ የገንዘብ ተቋማት የጋራ ደኅንነትን እና ሁሉን አካታች ብልጽግናን ለማምጣት ይረዳ ዘንድ የውሳኔ አሰጣጥ መዋቅራቸው ምሉዕነት ባለው መልክ የሚሻሻልበትን ሁኔታም አፅንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በይፋ ወደ ብሪክስ የተቀላቀለችው በ2015 ዓ.ም ሲኾን ኢኮኖሚያዊ ወዳጅነት ብቻ ሳይሆን ፍትሐዊ የኾነ፣ እኩልነት የሚሰፍንበት ብዝኃ ዋልታዊ ዓለምን ለመፍጠር ከሚተጉ ሀገራት ጋር በእኩል ደረጃ የተሰለፈችበት ስብስብ ነው ብለዋል።
እንደ ብሪክስ አባልነቷ ኢትዮጵያ እነዚህ ጥረቶች እንዲሳኩ በተለይም በዓለምአቀፍ ውሳኔ ሰጪ መድረኮች ለአዳዲስ ገበያዎች እና በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት ሰፋ ያለ ውክልና በሚገኝበት ሁኔታ ላይ በንቃት አስተዋፅኦ ታደርጋለች ነው ያሉት።
የብሪክስን እያደገ የመጣ ተፅዕኖ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሪክስ ከጠንካራ አዲስ ሀሳብ ተነስቶ ለዓለምአቀፍ ለውጥ የሚሠራ ብርቱ ኃይል ወደመኾን ተሸጋግሯል ብለዋል። አዳዲስ አባላት በመጨመራቸውም የጋራ ድምፃችን የበለጠ ይጠናከራል። የጋራ ዓላማችን የበለጠ ይጠራል። አቅማችንም ይሰፋል ማለታቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን