የምሥራቅ ዕዝ በብርሸለቆ የውትድርና ትምህርት ቤት ለ2ኛ ዙር ያሠለጠናቸውን የዕዙ መሪዎች አስመረቀ።

30

ፍኖተሰላም፡ ሰኔ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገር መከላከያ ሠራዊት የምሥራቅ ዕዝ የሠራዊት ሥነ ልቦና ግንባታ፣ የወታደራዊ እና የአመራር ሥልጠና የወሰዱ ከቲም መሪ እስከ ክፍለጦር ያሉ መሪዎችን ነው ያስመረቀው።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት የምሥራቅ ዕዝ ማሠልጠኛ ማዕከል አዛዥ ኮሎኔል አሊ ሰይድ የተሰጠው ወታደራዊ እና የአመራር ሥልጠና ከውስጥ እና ከውጭ ኾነው በየጊዜው ሕዝቡን ሰላም የሚያሳጡ እና የሀገርን ሉዓላዊነት የሚዳፈሩትን መመከት የሚያስችል ነው ብለዋል።

ሥልጠናው አሁን ላይ በአማራ ክልል ያለውን የጸጥታ ችግር ለመቅረፍ፣ የሕግ ማስከበር ሥራውን በውጤታማነት ለማሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መኾኑንም ገልጸዋል።

የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ እድሜአለም አንተነህ መከላከያ ሠራዊት በዞኑ ተከስቶ የነበረውን የጸጥታ ችግር በመቀልበስ ላደረገው አስተዋጽኦ ምሥጋና አቅርበዋል።

በአካባቢው ፈርሶ የነበረው መንግሥታዊ መዋቅር መልሶ እንዲቋቋም መሰዋዕትነት መክፈሉንም ጠቅሰዋል።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት የምሥራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ዕዙ ሀገርን ለማፍረስ የተነሱ ኀይሎች የሚያደርጉትን ሙከራ የሚያከሽፍ እና ከመበተን በመታደግ ከፍተኛ ተጋድሎ ያደረገ መኾኑን አንስተዋል።

ዕዙ በአማራ ክልል ባለው የጸጥታ ችግር በተለያዩ አካባቢዎች በመሰማራት ሕግ የማስከበር ሥራውን እየሠራ መኾኑን የገለጹት አዛዡ ሠልጣኞች የወሰዱትን ትምህርት በአግባቡ እንዲጠቀሙ አሳስበዋል።

ተመራቂ መሪዎች የነበራቸውን አቅም በማሻሻል እና ወቅቱ የሚጠይቀውን ትምህርት ከሥልጠናው ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በተለይም በየጊዜው ከውስጥ እና ከውጭ በመኾን የሀገርን ሉዓላዊነት የሚዳፈሩ ጠላቶችን መመከት የሚያስችል ሥልጠና ማግኘታቸውንም ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleርዕሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ እና የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ አረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ።
Next article“ብሪክስ ከጠንካራ አዲስ ሀሳብ ተነስቶ ለዓለምአቀፍ ለውጥ የሚሠራ ብርቱ ኃይል ወደ መኾን ተሸጋግሯል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)