
ባሕር ዳር: ሰኔ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ብሔራዊ የፍልሰት ምክር ቤት ዓመታዊ የምክክር መድረክ ግምገማ ተካሂዷል። መድረኩን አስመልክቶ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው መልዕክት አጋርተዋል።
ዛሬ ባካሄድነው የብሔራዊ የፍልሰት ምክር ቤት ዓመታዊ የምክክር መድረክ በፍልሰት ጉዳዮች ያከናወንናቸውን ተግባራት ገምግመናል።
ሀገራችን የውጭ ዜጎችን ተቀብላ በማስተናገድና ከለላ በመስጠት ረገድ ለረጅም ዘመናት የቆየና የዳበረ እሴት ያላት ናት፡፡
በአሁንም ጊዜ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ተቀብላ ጥበቃና ከለላ እያደረገች ትገኛለች፡፡
የፍልሰት ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብት፣ የሠላምና ደህንነት እንዲሁም የፖለቲካ፣ ዲፕሎማሲና የልማት ፖሊሲዎችን ቅርጽና ሁኔታዎችን በመበየን ላይ ይገኛል፡፡
ከዚህ አኳያ የሀገራችንን ሉዓላዊነት፣ ደህንነትና የመልማት ፍላጎት ከፍልሰተኞች ሰብዓዊ መብትና ክብር ጋር አመዛዝኖ መምራትን ይጠይቃል፡፡ ለዚህም የፍልሰትን በጎ ጎኖችን በማጎልበት ከኢኮኖሚ ሪፎርሙ ጋር አሰናስሎ መተግበር ይጠበቃል፡፡
ሀገራችን የፍልሰትን ጉዳይ በአስር ዓመቱ የልማት እቅዷ አካትታ እየተገበረች ትገኛለች፡፡ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን በቅንጅት መከላከል፣ በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ላይ የሚወሰደውን እርምጃ ማጠናከር፣ ሕጋዊ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪትን ምህዳር ማስፋት ይገባል፡፡
በተለይም በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ዜጎቻችንን ደህንነታቸውን እና ክብራቸውን በጠበቀ አኳኋን መመለስና በዘላቂነት ማቋቋም እንደሚገባም በዛሬው ስብሰባችን አቅጣጫ አስቀምጠናል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!