
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 24/2012 ዓ.ም (አብመድ) ሩዋንዳ የእንቅስቃሴ ገደቦችን ለማላላት ያሳለፈችውን ውሳኔ የጥናት ግኝቶችን መሠረት በማድረግ መሻሯን አስታውቃለች፡፡
በመሆኑም ከሌሎች አካባቢዎች ወደ ዋና ከተማዋ ኪጋሊ የሚደረጉ የትራንስፖርት አገልግሎቶች እና በሞተር ሳይክል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንደተከለከሉ ይቆያሉ፡፡ ይህም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በሀገሪቱ ያለበትን ደረጃ በተመለከተ በኅብረተሰብ ጤና ተቋማት በሚቀርብለት ምክረ ሐሳብ መሠረት የሀገሪቱ ካቢኔ እስከሚወስን ድረስ እንደሚጸና ታውቋል፡፡
በሩዋንዳ ወረርሽኙ ከገባበት መጋቢት እስከ ዛሬ ድረስ 370 ሰዎች በኮሮናቫይረስ እንደተያዙ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ በቫይረሱ ምክንያትም ባለፈው ቅዳሜ ለመጀመሪያ ጊዜ የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉን ሽንዋ ዘግቧል፤ 256 ሰዎች ደግሞ አገግመዋል፡፡
በሀገሪቱ ትናንት ግንቦት 23/2012 ዓ.ም ተጨማሪ 11 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡ ውጤቱ የሚያሳየው አሁንም ይበልጥ ጥንቃቄ ማድረግ እንጂ ክልከላዎችን ማላላት እንደማይገባ መሆኑን በመገንዘብም ሀገሪቱ ክልከላዎችን ለማላላት ከዚሀ ቀደም ያሳለፈቻቸውን ውሳኔዎች መሻሯን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡ ውሳኔውን ለማሻሻሏ የጥናት ግኝቶችንም እንደተጠቀመች ነው ዘገባው ያመላከተው፡፡
የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር እንደገለጸው በአዲስ ቫይረሱ የተገኘባቸው ከሌሎች ሀገራት የተመለሱ፣ ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎችና ነጋዴዎች ናቸው፡፡ ካለፈው አንድ ወር በፊት የኮሮናቫይረስ የተገኘባቸውም የውጭ ሀገራት የጉዞ ታሪክ ኑሯቸው በለይቶ ማቆያ ከነበሩ ሰዎች መሆኑን ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው፡፡
በአስማማው በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡
