
አዲስ አበባ: ሰኔ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) “በሀሳብ እንፎካከራለን፣ ስለሀገር እንተባበራለን” በሚል መሪ መልዕክት ነው ሁለተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን እያካሄደ የሚገኘው።
የኢዜማ ሊቀ መንበር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ፓርቲው የሀገርን ሁለንተናዊ ዕድገት መደገፍ የሚችል፣ የሕዝብ ውግንና መሠረት ያለው፣ በመርሕ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ ነው ብለዋል።
በተለይም ብዝኀ ሀሳብ የሚስተናገድበት የፖለቲካ ሥርዓት በመዘርጋት ሀገርን መምራት የሚችል ጠንካራ ፓርቲ ስለመኾኑም ነው ሊቀ መንበሩ ያረጋገጡት።
ኢዜማ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በሀሳብ መፎካከር የሚችል፣ እኩልነት፣ ፍትሐዊነት እና ዴሞክራሲ የነገሰበት አውድ በመፍጠር ነገ ሀገርን ተረክቦ መምራት የሚችል ፓርቲ ነው ብለዋል።
ፓርቲው ከተመሠረተ ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ቢገጥሙትም ችግሮችን በመቋቋም በሀገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መኾኑን የፓርቲው ሊቀ መንበር አንስተዋል።
በጉባኤው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን ጨምሮ ከ600 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።
ፓርቲው ለሁለት ተከታታይ ቀን በሚያካሄደው ጠቅላላ ጉባኤው የፓርቲ መሪዎች ምርጫን ጨምሮ የተለያዩ ውሳኔዎችን ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን