
ደብረ ብርሃን: ሰኔ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ በሰላም እሴት ግንባታ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በደብረ ብርሃን ምክክር እያደረገ ነው፡፡
ቢሮው ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም የሰላም ድጋፍ ተቋም ጋር በመተባበር ነው የፀጥታ እና የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ባካተተ መንገድ ውይይት እያደረገ የሚገኘው፡፡ ውይይቱ በማኅበረሰብ አቀፍ ግጭት አፈታት ስልት ላይ አተኩሮ የባለድርሻ አካላትን አቅም ለመገንባት ያለመ መኾኑም ተጠቁሟል፡፡
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የደብረ ብርሃን ከተማ ምክትል ከንቲባ ወርቃለማሁ ኮስትሬ በክልል ደረጃ ያጋጠመውን ቀውስ ለመፍታት የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች በጎ ተጽእኖ እያሳረፉ ነው ብለዋል፡፡
ሰላምን ለማምጣት ከፀጥታ ተቋማት በተጨማሪ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ያደረጉት የሰላም ግንባታ ሥራ የላቀ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በደብረ ብርሃን ከተማ እና አካባቢውም በሰላም ፈላጊ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድርሻ ዘላቂ ሰላምን ለማስቀጠል እና ፊታችንን ወደ ልማት እንድናዞር አድርጓል ብለዋል አቶ ወርቃለማሁ።
በቀጣይም የተሟላ ሰላም ለማስፈን እና የጸጥታ ችግሩን ለመቅረፍ ከነዚህ ወገኖች ግዙፍ ኀላፊነት በተሞላበት አግባብ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ የሚገባ ተግባር መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡
የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ደጀኔ ልመንህ ኢትዮጵያውያን ሰላምን በማስጠበቅ የቆየ ልምድ እና ባሕል ያለን ሕዝቦች ነን ብለዋል።
በግጭት እና በጦርነት ሀገርን ማስቀጠል አይቻልም፣ በሌሎች ሀገራት ልምድም በዚህ መንገድ ሀገር አልተገነባም ብለዋል አቶ ደጀኔ በመድረኩ ባቀረቡት መነሻ ጽሁፍ፡፡
ሁሉም ማኅበረሰብ ሰላምን ሊያስቀጥሉ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ መምከር እና የሰላም እሴቶችን አጥብቆ መገንባት እንደሚገባ ባቀረቡት ሰነድ ገልጸዋል፡፡
ከምክንያት ተላቅቀን የኛን ዘመን አሻራ ማሳረፍ ደግሞ ከዚህ ትውልድ የሚጠበቅ ኀላፊነት ነው ሲሊ ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ ከደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር እና ከሰሜን ሸዋ ዞን አሥተዳደር የተውጣጡ የፀጥታ አካላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ሌሎች የማኅበረሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን