
ባሕር ዳር: ሰኔ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከሚዲያ መሪዎች እና ባለሙያዎች ጋር የትምህርት የሚዲያ ፎረም ምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።
በምክክሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ቢሮው በተለያየ መልኩ ሪፎርም እያደረገ መኾኑን ተናግረዋል።
የትምህርት ቢሮ ዓላማ ሁለንተናዊ ስብዕናው የተሟላ ዜጋ፣ የረጅም ጊዜ ዓላማ ያለው፣ በስሜት ሳይኾን በስሌት የሚወስን፣ የሚደግፍ፣ የሚቃወም፣ ዘመኑን የዋጀ፣ ተወዳዳሪ፣ ሳይንሳዊ ዕውቀት ያለው፣ የቴክኖሎጂ አቅም ያለው የሰው ሃብት ማፍራት እና ሀገራችን በምታደርገው ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዞ አስተዋጽኦ ማበርከት ነው ብለዋል።
ዓላማችን ብቁ ሰብዓዊ ሃብት ማፍራት ነው ያሉት ኀላፊዋ ብቁ ሰብዓዊ ሃብት ማፍራት ካልተቻለ ተወዳዳሪ መኾን እንደማይቻል ነው የተናገሩት። በቴክኖሎጂ የተካነ ሰው ማፍራት ግዴታ መኾኑንም አንስተዋል።
በትምህርት ዘርፉ ከገጠመን ፈተና እንድንወጣ እና በትምህርት ሥራው ላይ የተፈጠሩ ችግሮች እንዲፈቱ የሚዲያ መሪዎች እና ባለሙያዎች እየሠሩ መኾናቸውን አመላክተዋል። ስለ ትምህርት ሁሉም ያገባኛል እንዲል፣ የልጆቻችን ዕጣ ፋንታ መወሰኛ ትምህርት መኾኑን እንዲረዳ፣ ትምህርትን የሚቃወም ሁሉ ጠላቴ ነው ብሎ ከጎናችን እንዲሰለፍ በተደረገው ጥረት የሚዲያ ሚና ከፍተኛ ነበር ነው ያሉት።
አሁንም ብዙ ሥራዎች እንደሚቀሩ ተናግረዋል። በትምህርት ላይ የነበረውን የተዛባ አስተሳሰብ እንዲቀረፍ አሁንም ትግል ያስፈልጋል ነው ያሉት። የትምህርት ሥራ የሌላ ዓላማ ማስፈፀሚያ እንዳይኾን መሥራት ይገባል ብለዋል።
በዚህ ዓመት በምዝገባ ያጣናውን በውጤት ለመካስ ጥረት እያደረግን ነው ያሉት ኀላፊዋ ለሚቀጥለው ዓመት ደግሞ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እየሠሩ መኾናቸውን አመላክተዋል። የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። የክረምት በጎ አድራጎት ቅድሚያ ለትምህርት እንዲሰጥ እያደረጉ መኾናቸውን እና ድርጅቶች ለትምህርት ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ እየሠራን ነው ብለዋል።
ቢሮው ባለፉት ዓመታት የባከነውን ለማካካስ አስቦ እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። የሚዲያ ተቋማት ሥራው ውጤታማ እንዲኾን ሥራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል። የተጎዱ ትምህርት ቤቶች እንዲጠገኑ እና ለትምህርት ዝግጁ እንዲኾኑ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። ማኅበረሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን