የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተማሪዎችና መምህራን ያለክፍያ በዲጂታል ቤተ መጽሐፍት እንዲጠቀሙ ተወሰነ፡፡

808

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 24/2012 ዓ.ም (አብመድ) የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተማሪዎችና መምህራን የኦንላይን መማር ማስተማር ሂደቱን እንዲያስቀጥሉ ሚኒስቴሩ አሳስቧል፡፡

የኮሮናቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና መቋረጡ ይታወቃል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎችና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የተቋረጠውን ትምህርት በቴክኖሎጂ አስደግፎ በኦንላይን የማስቀጠል እየተሠራ እንደሆነም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ሚኒስቴሩ እንደገለጸውም ትምህርት በኦንላይን ሲቀርብ የተማሪዎችን ኢኮኖሚያዊ አቅም በመገንዘብ በነፃ መጠቀም ለማስቻል ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር እየተሠራ ነው፡፡

በዚህ መሠረትም ከዛሬ ግንቦት 24/2012 ዓ.ም ጀምሮ የሚኒስቴር መስሪያ ወዳዘጋጀው የዲጂታል ቤተ መጽሐፍት ተማሪዎችና መምህራን ገብተው ሲጠቀሙ ከከፍያ ነፃ እንዲሆን መወሰኑን አስታውቋል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ኢትዮ ቴሌኮም ላደረገው ከፍተኛ ድጋፍ አመስግኗል፡፡ የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተማሪዎችና መምህራንም በ http://ndl.ethernet.edu.et/ አድራሻ በመግባት የነፃ አገልግሎቱን እንዲጠቀሙ ሚኒስቴሩ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጹ አስታውቋል፡፡ ተማሪዎችና መምህራን የኦንላይን መማር ማስተማር ሂደቱን በዚሁ አግባቡ እንዲቀጥሉም አሳስቧል፡፡

በኦንላይን ቤተ መጽሐፍቱ ከ80 ሺህ በላይ ማጣቀሻዎች፣ የመጀመሪያ ዓመት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሞጁሎች፣ በምስል የተደገፉ አጋዥ ማብራሪያዎች እንዲሁም የሁሉም የትምህርት ዓይነቶች መማሪዎች እንደሚገኙበትም ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው፡፡

Previous articleሚዛኑን የሳተው የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት እንዲስተካከል አብን ጠየቀ፡፡
Next articleሩዋንዳ ገደቦችን የማላላት ውሳኔዋን ሻረች፡፡