
ገንዳ ውኃ፡ ሰኔ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ2017/18 የምርት ዘመን ከታቀደው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ እስካሁን ከ22 ሺህ 300 ኩንታል በላይ ወደ መካዘን መግባቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ የግብዓት አቅርቦት እና ስርጭት ቡድን መሪ ዮናስ ባየ ተናግረዋል።
ቡድን መሪው 13 ሺህ 173 ኩንታል ዳፕ እና 9 ሺህ 156 ኩንታል ዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ዞኑ መግባቱን ነው ያስረዱት፡፡
ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስም ከ8 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች መሰራጨቱን አስረድተዋል።
ከተለያዩ የሰብል ዓይነቶች በምርት ዘመኑ ከ2 ሺህ 900 ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለማቅረብ ታቅዶ እስካሁን የበቆሎ እና የአኩሪ አተር ምርጥ ዘር መቅረቡን አቶ ዮናስ አብራርተዋል።
የበቆሎ ምርጥ ዘር ወደ ዞኑ ከገባው ከ220 ኩንታል በላይ ዘር 126 ኩንታል ለአርሶ አደሩ መሰራጭቱን ያነሱት ባለሙያው በተመሳሳይ የአኩሪ አተር ምርጥ ዘር የቀረበው 237 ኩንታል እንደተሰራጨ ነው የጠቆሙት።
አርሶ አደሮች ምርት እና ምርታማነትን ለመጨመር ሙሉ የግብዓት ፓኬጅ መጠቀም እንዳለባቸውም ባለሙያው አስገንዝበዋል።
የአፈር ማዳበሪያ በትክክል አርሶ አደሮች እጅ እንዲገባ ከዞን እስከ ቀበሌ ድረስ ጥብቅ ክትትል እና ቁጥጥር እየተደረገ መኾኑን አቶ ዮናስ ተናግረዋል።
አርሶ አደሮች የአፈር ማዳበሪያ ለቀጣይ ጊዜ በማሰብ ከቤታቸው እንዳያከማቹ የሚሰጣቸው ባላቸው ሄክታር ልክ እንደኾነም አመላክተዋል።
የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ግብርና ጽሕፈት ቤት የሰብል እና የግብዓት አቅርቦት ባለሙያ አማረ ተሻለ በ2017/18 የምርት ዘመን 2 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማስገባት ታቅዶ ወደ ሥራ የተገባ ሲኾን እስካሁን ከ740 ኩንታል በላይ ወደ መካዝን ገብቷል ነው ያሉት። ከዚህ ውስጥ 190 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቷል ብለዋል።
በምርት ዘመኑ ከ4 ሺህ 470 ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ባለሙያው ገልጸው በምርት ዘመኑም ከ116 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦቱ ከባለፈው ዓመት የተሻለ ስለኾነ ለአርሶ አደሮች በወቅቱ ተደራሽ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የአፈር ማዳበሪያ ቀድሞ እንዲደርስ መደረጉ ማሽላ እና ሌሎች በወቅቱ የሚዘሩ ሰብሎችን ከወዲሁ ቀድሞ ለመዝራት አስችሏል ሲሉ አርሶ አደሮች ተናግረዋል።
በቂ የኾነ ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት በመኖሩ ካለፈው ዓመት የተሻለ ምርት ለማግኘት እየሠሩ መኾናቸውን አርሶአደሮች ለአሚኮ ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን