የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ብቁ ፖሊስ ለመገንባት እየሠራ ነው።

64

ባሕር ዳር፡ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ ከጎንደር ከተማ፣ ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን እንዲሁም ከአድማ መከላከል ፖሊስ አመራሮች ጋር በጎንደር ከተማ ተወያይተዋል።

ኮሚሽነር ዘላለም በውይይቱ አንደገለጹት “በጥብቅ ዲሲፕሊን በመመራት በእውቀት፣ በሕዝብ አገልጋይነት ስሜት እና በክህሎት የበቃ ፖሊስ እንገነባለን” ብለዋል።

ሕዝብን ሰላም ለመንሳት በሚንቀሳቀሱ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ በመዉሰድ የተሰጣችሁን ተልዕኮ በድል መወጣት እንደሚገባ ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ እያካሄደ ያለው የሪፎርም ሥራ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ይታይ የነበረውን መቀዛቀዝ በማስቀረት ተቋሙን ወደ ነበረበት ከፍታ ለመመለስ የሚያስችል ነው በማለት ኮሚሽነር ዘላለም በአጽንኦት አብራርተዋል።

በሪፎርሙ ለአመራሩም ሆነ ለአባሉ ተከታታይነት ያለው የአቅም ግንባታ ሥልጠናን በመስጠት ዕውቀትን፣ አስተሳሰብንና ክህሎትን ማስተሳሰር፣ መቅረፅ እና ማስተካከል ላይ በትኩረት ይሠራል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በሪፎርም ሥራዎች፣ በስትራቴጂ፣ በመዋቅር እንዲሁም በአሠራር ረገድ እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራት ሲመዘኑ ስር-ነቀል ሪፎርም እየተካሄደ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ የክልሉ ፖሊስ ከነበረበት ችግር ወጥቶ የተሻለ የመፈፀም አቅም እንዲፈጥር የሚያስችል መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

የአማራ ክልል ፖሊስን በቴክኖሎጂ ብቁ ለማድረግ የሚያስችሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀምና ነባሮችን የማስፋት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ኮሚሽነሩ የአማራ ክልል ፖሊስን የሚያጠናክሩ ሥራዎችን በተለይም የፖሊስ ሠራዊት ግዴታው ብቻ ሳይሆን መብቱም በተገቢው መልኩ የሚከበርበት፤ እየተከናወኑ ባሉ የሪፎርም ሥራዎች ውጤት የሚመዘገብባቸውን የፕሮፌሽናሊዝም ሥራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

መረጃው የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ነው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየክልሉን አስተማማኝ ሰላም ለማረጋገጥ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት።
Next articleከ22 ሺህ 300 ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ዞኑ መድረሱን የምዕራብ ጎንደር ዞን አስታወቀ።