የክልሉን አስተማማኝ ሰላም ለማረጋገጥ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት።

21

ባሕር ዳር፡ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልልን አሁናዊ የሰላም ሁኔታ አስመልክቶ ከክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ እና የሰላም አማራጭን ከተከተሉ የቀድሞ ታጣቂዎች ጋር ቆይታ አድርገናል።

ከሐምሌ መጨረሻ/2015 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ በተፈጠረው ግጭት ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ደርሷል። ክልሉ ከገባበት ችግር እንዲወጣ መንግሥት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ሲያቀርብ ቆይቷል። በርካታ የታጠቁ ቡድኖችም የሰላም አማራጮችን ተቀብለዋል።

የሰላም ጥሪውን ከተቀበሉ ታጣቂዎች ውስጥ በለጠ አንዳርጌ ይገኝበታል። መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተከትሎ የሰላም አማራጭን መምረጡን ነው የገለጸው። ወደ ማኅበረሰቡ ከተቀላቀሉ ጀምሮ ደግሞ በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ነግሮናል። ወጣቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄደው ግጭት የክልሉ ሃብት መውደሙን እና አምራች ወጣቶችም ሕይዎታቸውን አጥተዋል ብሏል።

በተራዘመ ግጭት በክልሉ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለማስቀረት አሉኝ ያላቸው ጥያቄዎች በውይይት መልስ እንዲያገኙ የሰላምን መንገድን እንዲከተል መገደዱን ገልጾልናል። ሌሎች በጫካ የሚገኙ ወገኖችም መንግሥት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ ተቀብለው ጥያቄዎቻቸውን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ እንዳለባቸው መክሯል።

ሌላኛው የሰላም አማራጭን የተከተለው ጸዳሉ ደሴ ከዚህ በፊት የክልሉ ሕዝብ ይደርስበት የነበረውን ችግር፣ የልማት እና ሌሎች ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ተጠይቆ መፍትሔ ባለመሰጠቱ ወደ ጫካ ለመግባት መገደዱን ገልጿል።

ይሁን እንጅ የመረጠው መንገድም የክልሉን ሕዝብ ይበልጥ ችግር ውስጥ የሚጥል ኾኖ ማግኘቱን ነው የገለጸው። ይባስ ብሎ አሁን ላይ ደግሞ ቡድኑ ከአማራ ሕዝብ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ጭምር አጋርነት በመፍጠር እየሠራ ያለው ሥራ አማራን ለዳግም ጥፋት የሚያጋልጥ ኾኖ በማግኘቱ የሰላም መንገድን ለመምረጥ መገደዱን ገልጿል። ክልሉ ከገባበት ምስቅልቅል እንዲወጣ የታጠቁ ኃይሎች የሰላም አማራጭን እንዲመርጡ፣ በውጭ የሚኖሩ ኃይሎችም የሚያራግቡትን የሃሰት ወሬ በመተው ለሰላም እንዲሠሩ ጥሪ አቅርቧል።

የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) እንደገለጹት ደግሞ ባለፉት ሁለት ዓመታት ታጣቂ ቡድኑ በማኅበረሰቡ ላይ እገታ እና ዘረፋ ፈጽሟል፤ የግብርና ግብዓት ጭምር በመዝረፍ አርሶ አደሮች እንዳያመርቱ እንቅፋት ኾኗል፤ ተማሪዎችም ከትምህርት ገበታ እንዲፈናቀሉ በማድረግ የትውልድ ክፍተት እንዲፈጠር አድርጓል፤ በሀገር ሽማግሌዎች ላይ ጭምር ከማኅበረሰቡ እሴት ያፈነገጠ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ፈጽሟል።

መንግሥት የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ የሰላም አማራጭን ባልተከተሉ ቡድኖች ላይ በወሰደው የሕግ ማስከበር ሥራ ቡድኑ ይገኝባቸው የነበሩ ቦታዎችን ሰላም በማድረግ ወደ መደበኛ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል። ማኅበረሰቡም የቡድኑን ሥራ እየተረዳ በመምጣቱ ከመንግሥት ጎን ተሰልፎ እየታገለ መኾኑንም ገልጸዋል።

የሰላም አማራጭ የተከተሉ ኃይሎችን ደግሞ ጥያቄዎቻቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲያቀርቡ በክልሉ የሰላም ካውንስል ጭምር ተቋቁሞ ሢሠራ መቆየቱን ገልጸዋል።

በተሠራው ሥራም በርካታ ቁጥር ያለው የታጠቀ ኃይል የሰላም አማራጭን መከተሉን ገልጸዋል። መንግሥት የሰላም አማራጮችን የተከተሉ ኃይሎችን በተለያዩ ማሠልጠኛ ማዕከላት በማሠልጠን እና የመቋቋሚያ ገንዘብ በመሥጠት ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ አድርጓል። ለዚህ ደግሞ ደንብ ወጥቶ እየተሠራ መኾኑን ነው ያነሱት።

አሁን ላይም የሰላም አማራጭን ለተቀበሉ የታጠቁ ኃይሎች ሥልጠና ለመሥጠት ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል። በቀጣይም የሰላም አማራጭን ለሚቀበሉ ወገኖች በቅርበት ለማሠልጠን እንዲያመች ተጨማሪ የማሠልጠኛ ማዕላትን በተለያዩ አካባቢዎች ለመክፈት ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

የክልሉን አስተማማኝ ሰላም ለማረጋገጥ እና መልካም አሥተዳደር ለማስፈን አሁንም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ክልሉ ወደ ቀደመ የተሟላ ሰላሙ እንዲመለስ ደግሞ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ያልተጠናቀቁ የልማት ሥራዎችን ለማጠናቀቅ እና አዳዲስ ተግባራትን ለመፈጸም እየተሠራ ነው።
Next articleየአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ብቁ ፖሊስ ለመገንባት እየሠራ ነው።