አባቶች የተሰጣቸውን ጸጋ በመጠቀም ለሰላም መስፍን በትኩረት እንዲሠሩ ‎የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ አሳሰበ።

18

ጎንደር: ሰኔ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ‎የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ በሀገር በቀል የግጭት አፈታት እና በሰላም ግንባታ ዙሪያ ከተለያዩ ዞኖች እና ወረዳዎች ለተወጣጡ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በጎንደር ከተማ የግንዛቤ ማሰጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል።

ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ሚና ከፍተኛ ነው ያሉት የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ አባቶች የተሰጣቸውን ጸጋ በመጠቀም ለሰላም መስፈን በትኩረት እንዲሠሩ አሳስበዋል።

‎በክልሉ የተፈጠረዉ የሰላም እጦት ስርቆት፣ እገታ እና ጽንፈኝነት እንዲበራከት በር ከፍቷል ያሉት ኀላፊው ይህን ለመከላከል የዜጎች የመወያየት እና የመመካከር ባሕል እንዲዳብር እንዲሠሩም ጠይቀዋል። ‎መንግሥት የአማራ ሕዝብ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን ለመፍታት አቋም ይዞ እየሠራ መኾኑንም አንስተዋል።

‎ሰላም እና አብሮነትን ለማጠናከር ለፍትሕ መቆም፣ ሰላማዊ አመለካከትን መገንባት እንዲሁም ይቅርታ እና ይቅር ባይነትን ማጠናከር ያስፈልጋልም ብለዋል። ስንታረቅም ኾነ ስናስታርቅ እውነተኛ፣ ፍትሐዊ፣ ምሕረትን እና ሰላምን የሚያወርድ እንዲኾን የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሠሩም አመላክተዋል።

ኢትዮጵያን ለማዳከም ከጥንት ጀምሮ የውጭ ወራሪዎች ሲሠሩ እንደነበር በሥልጠናው ያገኘናቸው አቶ ወልዴ መና አስታውሰዋል። አሁንም የኢትዮጵያውያንን አብሮነት የማይሹ የውጭ ጠላቶች የዜጎችን የእርስ በእርስ አንድነት ለመሸርሸር የውስጥ ጠላቶችን በማሰለፍ እየሠሩ ነው ብለዋል።

አስተያየት ሰጭው ‎ ይህን ችግር ለመቅረፍ እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በተለይ የሀገር ሽማግሌዎች የግጭት አፈታት ልምዳቸውን በመጠቀም በስፋት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አስረድተዋል። ‎ወጣቶች የሰላም ባለቤት እንዲኾኑ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ የተናገሩት ደግሞ አቶ ብርሃኑ በለጠ ናቸው። በሥልጠናው ያገኙን ሀሳብ ከሀገር በቀል ዕውቀት ጋር በማጣመር ለሰላም መስፈን እንደሚሠሩም አንስተዋል።

ዘጋቢ:- አዲስ ዓለማየሁ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየጽንፈኛውን ሕልውና ለማክሰም ከሕዝብ የመነጠል እና የሃብት ምንጮችን የማምከን ሥራ እየተሠራ ነው።
Next articleበአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ያልተጠናቀቁ የልማት ሥራዎችን ለማጠናቀቅ እና አዳዲስ ተግባራትን ለመፈጸም እየተሠራ ነው።