ሚዛኑን የሳተው የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት እንዲስተካከል አብን ጠየቀ፡፡

264

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 24/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) “አምነስቲ ኢንተርናሽናል” ያቀረበዉ ሪፖርት የሚጠበቅበትን ሙያዊ ገለልተኝነት ያልተከተለ መሆኑን አስታውቃል፡፡

“አምነስቲ ኢንተርናሽናል” ከሰሞኑ ያወጣው ሪፖርት ቀደም ሲል ሲያወጣቸው ከነበሩ በአንፃራዊነት የተሻለ ገለልተኝነት ከነበራቸው ሪፖርቶች በተለየ መልኩ የተጠናቀረ መሆኑን አብን በመግለጫው አመላክቷል፡፡ ሪፖርቱ በደል የደረሰበትን ወገን በበዳይነት ፈርጆ ማቅረቡ ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም ነው አብን ያመላከተው፡፡ ይህም በተለይም ለሰብአዊ መብቶች ጥበቃ እሰራለሁ ከሚል ተቋም ፍፁም የማይጠበቅ እንደሆነ በመግለጽ ኮንኖታል፡፡

ሪፖርቱ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አራምዳቸዋለሁ ከሚላቸዉ ከእውነት፣ ከፍትሕና ከሰብዓዊነት መርሆዎች በተፃራሪ የተጠናቀረ መሆኑም ተቋሙ አለኝ ለሚለው አጠቃላይ ተዓማኒነት ትልቅ ፈተና እንደሚሆን ነው ንቅናቄው የገለጸው፡፡ ለአንድ ወገን ያዳላው ሪፖርቱ ደርጅቱን፣ ለሰብአዊ መብቶች መከበር በሃቅ ተግተው የሚሰሩ ወገኖችን እንዲሁም ጥቃት የደረሰባቸውን ወገኖች በእጅጉ ያሳዘነ መሆኑንም አብን በመግለጫው አስታውቋል፡፡

ከሚዛናዊነት መጓደል ባለፈ አምነስቲ ማካተት እየተገባው ያላካተታቸው ለአብነትም በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የንጹሃን ሕይዎት ያለፈባቸው ድርጊቶች፣ የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እገታ፣ የዜጎች ማፈናቀልና እንግልቶች… መኖራቸውን ጠቅሷል፡፡ በተቋሙ ውስጥ ያለው የፖለቲካ አሰላለፍ ወገንተኝነትና በሴራ የተሰማሩ ግለሰቦች መኖራቸው ለዚህ ምክንያቶች መሆናቸውን እንደሚገነዘብም ንቅናቄው አመላክቷል፡፡

በዚህ ረገድ “አምነስቲ ኢንተርናሽናል” ጉዳዩን በጥልቀት በመመርመር ተገቢውን የእርምት እርምጃ ይወስዳል ብሎ ተስፋ እንደሚያደርግ አብን አስታውቋል፡፡ በመሆኑም የቀረበዉ ሪፖርት ያለበትን ጉልህ ስህተት እና ጥፋት በአግባቡ መርምሮ እና ተገንዝቦ የማያሰራ በሚል እንዲያነሳው እና በምትኩ በትክክል እና በገለልተኛ ሁኔታ ሪፖርቱን እንዲያጠናቅር የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አሳስቧል፡፡

ንቅናቄው በዜጎች ላይ በየትኛውም አካባቢና ሁኔታ የሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መቆም አንዳለባቸ በማሳሰብም ለዚህም የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል፡፡

Previous articleሁለት የራያ ቆቦ ወረዳ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ህግ በማስከበር ላይ እያሉ ሕይወታቸው አለፈ።
Next articleየከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተማሪዎችና መምህራን ያለክፍያ በዲጂታል ቤተ መጽሐፍት እንዲጠቀሙ ተወሰነ፡፡