
ሁመራ፡ ሰኔ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጦርነት የሚፈታ ችግር ባለመኖሩ ተፋላሚ ኀይሎች በመስማማት የክልሉን ሰላም ወደ ነበረበት ሊመልሱ እንደሚገባ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የሁመራ ከተማ ነዋሪዎች ጠይቀዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ በተከሰተው ግጭት ሳቢያ ሕዝቡ በርካታ ችግሮች እየደረሰበት ነው ያሉት ነዋሪዎቹ ከጦርነት የሚገኝ ትርፍ ባለመኖሩ መንግሥት፣ ኅብረተሰቡ እና በጫካ ያሉ ኀይሎች ወደ ጋራ መፍትሔ መሄድ አለባቸው ነው ያሉት።
የሁመራ ከተማ ነዋሪው ጀጃው አበራ ይሄ ግጭት ወንድም ለወንድም የሚያገዳድል ነው። ከዚያም በላይ ትውልዱ ላይ ከፍተኛ ጫና እያደረሰ ነው። ለዚህም በክልሉ ከ4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸው አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።
ከሁሉም ወገን ያሉ ጉድለቶችን አምኖ በማረም ለሕዝቡ እፎይታ መስጠት እንደሚገባም ገልጸዋል። በክልሉ ያለው የሰላም እጦት እንደሚያሳስባቸው ያነሱት ደግሞ ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ብርሃኑ ጠጋ ናቸው። በሰላም እጦቱ ምክንያት በክልሉ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ አስቸጋሪ መኾኑን አመላክተዋል።
ታጣቂ ኀይሎች ለሕዝብ የሚያስቡ ከኾነ እየደረሰ ያለውን ችግር በመረዳት የመንግሥትን የሰላም ጥሪ እንዲቀበሉም ጠይቀዋል።ሰላም ከሌለ ኹሉም ነገር የለም ያሉት ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ መሰሉ ታሉ ኅብረተሰቡ ልጆቹን በመምከር ካላስፈላጊ እንቅስቃሴ ሊጠብቃቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።
በጦርነት የሚፈታ ችግር የለም ፣ ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ በተከሰቱ ጦርነቶች የደረሰው ውድመት ሊያስተምረን ይገባል ነው ያሉት። የክልሉን ሰላም በትብብር በመመለስ በሰው እና በንብረት ላይ የሚደርሰውን ውድመት እና ኪሳራ ማዳን እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።
የሁመራ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ እንኳየነህ ሙሉ የዞኑ እና የከተማው ሕዝብ የሰላም ዘብ መኾኑን አንስተዋል። ሕዝባችን የሰላምን ጥቅም ይረዳዋል፣ የጦርነትን ዳፋም ይገነዘባል ያሉት ከንቲባው የከተማችንን ሰላም በተደራጀ ኹኔታ እየጠበቅን ነው ብለዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው ንግግር የሁሉም ችግሮቻችን መፍቻ ቁልፍ መኾኑን እናምናለን ነው ያሉት። የግጭትን እና የጦርነትን ዳፋ እንገነዘባለን ያሉት አሥተዳዳሪው የትኛውም ኀይል ከጦርነት ይልቅ የሰላም አማራጭን ቢከተል የተሻለ መኾኑን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያን ለማሻገር እና የአማራን ችግሮች ለመፍታት መፍትሔው ሰላማዊ ንግግር በመኾኑ ጥያቄ አለኝ የሚል አካል የሕዝቡን ሁለንተናዊ መሥተጋብር የማይጎዳውን የሰላም መንገድ ሊመርጥ እንደሚገባም አመላክተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን