
ደብረ ታቦር: ሰኔ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኅብረተሰቡን ተሳትፎ በማጠናከር የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም ለማጽናት በትኩረት እየሠራ መኾኑን የደቡብ ጎንደር ዞን አስታውቋል። የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ የሰላም አማራጭ የብልህነት መንገድ በመኾኑ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በአማራ ክልል በተፈጠረው ግጭት መሠረተ ልማቶች ወድመዋል፤ ሕፃናትም ከትምህርት ገበታቸው ተለይተው ስነልቦናዊ ጫና ደርሶባቸዋል ነው ያሉት። ከሰላም ተቃራኒ የቆሙ ቡድኖች ጥያቄ አለን በማለት በማኅበረሰቡ ላይ የተለያዩ ጉዳቶች መፈጸማቸውንም ገልጸዋል።
የግል ፍላጎትን ለማሟላት የአማራን ሕዝብ ጥያቄ ተገን በማድረግ ማኅበረሰብን መበደልና ማንገላታት ሁሉም ሊያወግዘው የሚገባው ድርጊት ነው ብለዋል። የመረጡት መንገድ የማይጠቅም መኾኑን በመገንዘብ መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀበልው የስላም መንገድን የመረጡ አካላት መኖራቸውንም ተናግረዋል።
ወደ ማኅበረሰቡ ሲቀላቀሉም በሥራ ተሰማርተው ልማትን እንዲያለሙ፣ የአካባቢ ሰላምን እንዲያሰፍኑም እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም በዘላቂነት ለማጽናት ወረዳን፣ ቀበሌን እና ቀጣናን መሠረት ያደረገ የገጽ ለገጽ ውይይቶች መካሄዳቸውን አንስተዋል።
ለሰላም ሁሉም ሰው ባለድርሻ መኾኑን በመገንዘብ በጋራ መሥራት እንደሚገባው ዋና አስተዳዳሪው አሳስበዋል። ማኅበረሰቡ የግጭትን አስከፊነት ተረድቶ በአደባባይ ወጥቶ ከመንግሥት ጎን እንደሚመቆም መግለጹንም ተናግረዋል።
ማኅበረሰቡ አደባባይ በመውጣት ልማት እንፈልጋለን፣ ልጆቻችን በትምህርት ገበታቸው ይዋሉ የሚሉ ሃሳቦችን በመሰንዘር ሰላምን ፈላጊ መኾኑን እንዳረጋገጠ ተናግረዋል። ወጥ ሀገራዊ ትርክትን በማጽናት፣ የእኔ ከሚል ሃሳብ በመውጣት ሀገርን በልማት ማስቀጠል እንደሚገባም አመላክተዋል። ማንም በማንም መስዕዋትነት መኖር የለበትም ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው የጋራ በኾነ ስምምነት ላይ ተመሥርቶ ሰላምን በማስጠበቅ ሀገርን መገንባት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን