
አዲስ አበባ: ሰኔ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኮሚሽኑ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት በኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በትግራይ ክልል በተሟላ ሁኔታ ሂደቱን ለማስጀመር ከክልሉ ጊዜያዊ አሥተዳደር እና አጋር አካላት ጋር ውይይቶችን እያካሄደ መኾኑን ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ክልሉ አመቺ ሁኔታ ላይ አለመኾኑንም ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል።
የምክክር ሂደቱን አካታች እና አሳታፊ ከማድረግ አኳያ በኮሚሽኑ የምክክር ሂደት ሲሳተፉ ቆይተው አቋርጠው የወጡ እና እስካሁን ያልተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲካተቱ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ እና በፍርድ ሂደት ላይ ያሉትን ለማሳተፍ በኮሚሽኑ በኩል የሚደረገው ጥረት መቀጠሉን ነው ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው የገለጹት።
አቶ ጥበቡ ከዲያስፖራዎች አኳያም በቀጣይ ጊዜያት በተለያዩ አሕጉራት አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራውን እንደሚሠራ ተናግረዋል። የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራውን ቀጣይነት ማረጋገጥ፣ የአጀንዳ ቀረፃ እና ዋናውን የምክክር ጉባኤ ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየሠራ ነውም ተብሏል።
ቀጣይ ሥራዎችን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት በተለይም ከምሁራን ጋር ተቀራርቦ የመሥራት፣ ወጣቶች፣ ሴቶች እና አካል ጉዳተኞችን ትርጉም ባለው መንገድ እንዲካተቱ ብቻ ሳይኾን ተሳታፊ እንዲኾኑም እንደሚደረግ ተናግረዋል። ዋናው የምክክር ጉባኤ መካሄድ ሲጀመር ከ4 ሺህ 500 የማያንሱ ተሳታፊዎች እንደሚኖሩት በመግለጫው የተጠቀሰ ሲኾን ትኩረት የሚደረግባቸው አጀንዳዎች ወደፊት እንደሚገለጹ ተመላክቷል።
ዘጋቢ:- ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን