የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ጤና ተቋማት እውቅና ተሰጥቷል።

15

ባሕር ዳር: ሰኔ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ደሴ ቅርንጫፍ በ2017 ዓ.ም የላብራቶሪ ጥራት ማሻሻያ መርሐ ግብር የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ጤና ተቋማት እውቅና ሰጥቷል። በእውቅና መርሐ ግብሩ ላይ በቅርንጫፉ የሚደገፉ የሆስፒታል እና የጤና ጣቢያ ኀላፊዎች እና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

ከባለፈው ዓመት የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡት የኮምቦልቻ እና ከሚሴ ጤና ጣቢያዎች የተገልጋዎችን ርካታ ለማሳደግ እንደሚሠሩ ለአሚኮ ተናግረዋል። የእውቅና መርሐ ግብር መካሄዱ ለተሻለ ሥራ እንደሚያነሳሳቸው የጤና ጣቢያዎቹ ላቦራቶሪ አስተባባሪዎች ገልጸዋል።

በአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የደሴ ቅርንጫፍ የሕክምና ላብራቶሪ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሐብታሙ መኮንን የተሻለ አፈፃፀም ላመጡ የጤና ተቋማት እውቅና መሰጠቱን አንስተዋል። እውቅና መስጠት የተጀመረው ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ መኾኑን ያነሱት አቶ ሐብታሙ በወቅቱ 9 የጤና ተቋማትን በላብራቶሪ ጥራት አሥተዳደር ከደረጃ ሁለት እስከ አራት ማግኘታቸውን አስታውሰዋል።

ዘንድሮም በስድስቱ ዞኖች ከሚገኙ ጤና ተቋማት በተለያዩ ደረጃዎች እውቅና ተሰጥቷቸዋል ብለዋል። በሕክምናው ዘርፍ ላብራቶሪ ወሳኝነት ያለው በመኾኑ በግብዓት ማጠናከር ይገባል ያሉት በአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የደሴ ቅርንጫፍ ዳይሬክተር አንተነህ ደመላሽ የጤና ተቋማት ዓለም አቀፍ ደረጃን እንዲያሟሉ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የጤና ተቋማት ለተገልጋዎች የተሻለ ሕክምና እንዲሰጡ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ይሻል ያሉት ደግሞ በአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የላብራቶሪዎች አቅም ግንባታ ዳይሬክተር የምስራች ዓለሙ ናቸው። በክልሉ ያሉ ጤና ተቋማትን በአቅም እና በግብዓት እየደገፈ መኾኑን የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ጠቁመዋል።

በዓለም አቀፍ የሕክምና ላቦራቶሪ የቲቢ ጅን ኤክስፐርት ውስን ምርመራ የደረጃ ምዘናን ያሟሉት የደሴ እና ወልድያ ኮምፕሬኸንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች፣ ቅዱስ ላሊበላ ጠቅላላ ሆስፒታል እና ደብረ ብርሃን የሚገኘው ደነባ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ናቸው።

ዘጋቢ፡- ሰልሀዲን ሰይድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleክልሉን የልማት ማዕከል ለማድረግ ለሰላም እንደሚቆሙ በአዋበል ወረዳ የወጀል ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
Next articleየውኃ ወለድ በሽታዎችን እንዴት መከላከል ይቻላል ?