
ባሕርዳር፡ ሰኔ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 48ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም ዐቀፍ የልማት ማኅበር ጋር ለሁለተኛው ዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ የዕድገት ልማት ፖሊሲ ማስፈፀሚያ የሚውል 258,100,000 ኤስ.ዲ.አር እና ለፍጥነት መንገድ ልማት ድጋፍ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል 27,300,000.00 ኤስ.ዲ.አር የፋይናንስ ድጋፍ እና የብድር ስምምነቶችን ለማጽደቅ በቀረቡ ሁለት ረቂቅ አዋጆች ላይ ነው፡፡
ሁለቱም ብድሮች ከወለድ ነጻ፣ 0.75% የአገልግሎት ክፍያ የሚከፈልባቸው ሆኖ የ6 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በረጅም ጊዜ የሚከፈሉ ናቸው፡፡ ምክር ቤቱም የብድር ስምምነቶቹ ከሀገራችን የብድር አሥተዳደር ስትራቴጂ ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን በማረጋገጥ በሙሉ ድምጽ አጽድቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል፡፡
በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የፌዴራል የገቢ ግብር አዋጅን ለማሻሻል የወጣ አዋጅ ላይ ነው፡፡ ቀደም ሲል ሲሰራበት የነበረው የፌዴራል የገቢ ግብር አዋጅ አሁን ከምንገኝበት ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ ሁኔታ አንጻር ሲታይ በርካታ ክፍተቶች ያሉበት በመሆኑ የአዋጁን ድንጋጌዎች በማሻሻል የታክስ ስርአቱ መሠረታዊ የታክስ መርሆዎችን ለማሳካት በሚያስችል መልኩ እንዲቀረጽ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የማሻሻያ አዋጁ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በማሻሻያ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ በሙሉ ድምጽ አጽድቆ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡
በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው ከናይጄሪያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ጋር የዲፕሎማቲክ እና የሰርቪስ ፓስፖርት ለያዙ ሰዎች ቪዛን ለማስቀረት በተፈረመው የሁለትዮሽ ስምምነት ላይ ነው፡፡ ስምምነቱ የዲፕሎማቲክ እና የሰርቪስ ፓስፖርት የያዙ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ዲፕሎማቶች እና ዜጎች ለሥራ ጉዳይ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ቪዛ ለማግኘት የሚያስፈልጉትን ቅድመ ሁኔታዎችና የሚወስደውን ጊዜ በማስቀረት እንዲሁም የሁለትዮሽ ግንኙነቱን በማጠናከር ረገድ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው በመታመኑ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በስምምነቱ ላይ ከተወያየ በኋላ በሙሉ ድምጽ አጽድቆ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን