በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።

15

ባሕር ዳር: ሰኔ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የ2017 በጀት ዓመት የፓርቲ እና የመንግሥት ሥራዎች ዓመታዊ የማጠቃለያ ግምገማ እንዲሁም የቀጣይ 90 ቀናት እቅድ ኦሬንቴሽን መድረክ አካሄዷል።

የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የከተማዋ ወጣቶች ችግር ፈጣሪ ሳይኾኑ ሰላም አምጭ፣ የመፍትሔም አካል መኾናቸውን አድንቀው በአጠቃላይ የሰላም ተዋናይ የኾኑትን እካላት ሁሉ አመስግነዋል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አያይዘውም የገቢ አሰባሰብን ዘምናዊ ለማድርግ እየተሠራ ነው ብለዋል። በከተማዋ የሚመነጨው ገቢ በጥልቅ ተገምግሟል ያሉት አቶ ጎሹ በከተማዋ እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ 5 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብስብ መቻሉንም ጠቅሰዋል።

ባሕር ዳር በጣና ሐይቅ እና ዓባይ ወንዝ ዳርቻ በመገኘቷ ተፈጥሮ አብዝቶ ያደላትን ገጽታ በማዋደድ ልማቷን ለሰው ልጆች በሚስማማ መልኩ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት። እንዲህ በመሠራቱም የማኅበረሰቡ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ማኅበራዊ እና ባሕላዊ ትስስር ጨምሯል ብለዋል።

ወጣቶች በአልባሌ ሥፍራ ከሚውሉበት ጠንቅ ውስጥ እንዲወጡ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት አቶ ጎሹ። ዘመናዊ ካፍቴሪያዎች፣ የፋስት ፉድ መሽጫ ሱቆች መሠራታቸውንም ተናግረዋል።

በከተማዋ 15 አረንጓዴ ፓርኮች የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ ተሠርተዋል፤ ይህም ለ476 ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥሯል ነው ያሉት።

ለ11 ዓመታት ቆሞ የቆየውን የባሕር ዳር ቄራ አገልግሎት የማስፋፊያ ሥራን በማከናወን በአዲሱ ዓምት አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ እየተሠራ ነውም ብለዋል። በዚህም የእንስሳት መኖን በማምረትና ወደ ውጭ ሀገር በመላክ የውጭ ምንዛሬ ያስገኛል ነው ያሉት።

የቤት ማኅበርን ተግባራዊ ማድረጋቸውን የገለጹት አቶ ጎሹ እስካሁን 22 ሺህ የመንግሥት እና የልማት ድርጅት ሠራተቶች በማኅበር ተደራጅተው ቦታ ለመውሰድ መመዝገባቸውን አውስተዋል። አሁን ላይ በሦሥት ቦታዎች የሳይት ልየታ ተደርጓል። ካርታ ተሰርቶ በማጽደቅ የካሳ ክፍያው እየተሠራ ነው። በመኾኑም በማኅበር ተደራጅተው ቦታ ለጠየቁ የከተማዋ የማኅበረሰብ ክፍሎች “ከቻልን በዚህ ዓመት ካልቻልን በሚቀጥለው ዓመት መሬቱን ለማስተላለፍ ዝግጅቱ ተጠናቋል” ብለዋል።

ሌሎችን የከተማዋ ነዋሪዎችም የቤት መሥሪያ ቦታ ባለቤት የማድረግ ሥራ በቀጣይ ይተገበራል ነው ያሉት።

ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበ2018 በጀት ዓመት ካለፈው በላቀ ለመሥራት እና የከተማዋን ሰላም ለመጠበቅ በሰፊው ታቅዷል።
Next articleየሚኒስትሮች ምክር ቤት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ ።