
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞላ ሁሴን ባለፉት ሁለት ዓመታት እንደ ክልል የገጠመውን ችግር ለመፍታት በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።
ችግሮችን ለመፍታት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ማወያየታቸውንም ነው ኀላፊው የተናገሩት።
ከውይይቱ ማግሥት ማኅበረሰቡ የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ችግር ፈቺ ኾኗል፤ በዚህም ከፍተኛ የሚታይ ለውጥ መጥቷል ብለዋል።
አቶ ሞላ አክለውም ኅብረተሰቡን ስለ ሰላም ጥቅም እና ጉዳት በማወያየት የጋራ ግንዛቤ በማስጨበጥ የከተማዋ ነዋሪችን የሰላም ጠባቂ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።
ባሕር ዳር ከተማ አኹን ላይ በአስተማማኝ ኹኔታ ወደ ሰላም ተመልሳለች ያሉት አቶ ሞላ ከሌላው ጊዜ በተለየ ኹኔታ ከተማዋን የቱሪስት መስህብ ማድረግ ስለመቻሉም አስገንዝበዋል።
በመኾኑም በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኝዎች በመጎብኘት ላይ ይገኛሉ ነው ያሉት። በ2017 በጀት ዓመት በከተማዋ ስለነበረው የመልካም አሥተዳደር እና ፖለቲካዊ ሥራዎች ዙሪያ ከሕዝቡ ጋር ለመምከር ተዘጋጅተናልም ብለዋል።
በ2018 በጀት ዓመት ከ2017 በጀት ዓመት ከተሠራው ሥራ በላቀ ኹኔታ ለመሥራት እና የከተማዋን ሰላም በማይናወጥ ኹኔታ ለመጠበቅ በሰፊው ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል ነው ያሉት።
ሰላም የሚጸናው፣ ልማት የሚሰፍነው እና መልካም አሥተዳደር የሚረጋገጠው ሕዝብን አሳታፊ ማድረግ ሲቻልም ነው ብለዋል።
መሪዎች ቀበሌ ድረስ ወርደው በ2017 ዓ.ም ምን እንደሠሩ እና በተገኘው ውጤት ዙሪያ ከሕዝቡ ጋር ፊት ለፊት ይወያያሉ፤ ግምገማም ያደርጋሉ ነው ያሉት።
በሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን