በከተማ አሥተዳደሩ ከ234 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች የጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ ኾነዋል።

6

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎት የተሻለ አፈጻጸም የነበራቸው ክፍለ ከተሞች ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል። ዕውቅና ከተሰጣቸው ክፍለ ከተሞች ውስጥ የጣና ክፍለ ከተማ አንዱ ነው።

የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ጌትነት ካሴ እንዳሉት በተያዘው በጀት ዓመት በክፍለ ከተማው የጤና መድኅን ተጠቃሚ ለማድረግ ከታቀደው 11 ሺህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ 98 በመቶውን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።

በቀጣይም የጤና መድኅን ተጠቃሚ ያልኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ ሲስተር ዓለም አሰፋ ጤናማ እና አምራች ዜጋ ለመፍጠር የማኅበረሰብ ጤና መድኅን ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት።

በከተማ አሥተዳደሩ በ2017 በጀት ዓመት ከማኅበረሰቡ ከ54 ሚሊዮን 867 ሺህ ብር በላይ ማሠባሠብ ተችሏል። ከ234 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችም አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።

ከግብዓት ጋር የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ከተማ አሥተዳደሩ በ2018 ዓ.ም የከተማ መድኃኒት ቤቶችን ለማስጀመር እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎት መረዳትን መሠረት ያደረገ መኾኑን ያነሱት ኀላፊዋ ከፍለው ለመታከም አቅም የሌላቸውን ዜጎች ተጠቃሚነት ለማሳደግ ማኅበረሰቡ የጤና መድኅን አባል እንዲኾን አሳስበዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በከተማ አሥተዳደሩ የጤና መድኅን አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

ከተማ አሥተዳደሩ በጤና መድኅን አገልግሎት የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገቡንም አንስተዋል። ለጤና መድኅን መሻሻል የባለሃብቶች ድርሻ ከፍተኛ እንደነበርም ገልጸዋል።

ለአንድ ሀገር እድገት ትልቁ ሃብት ሰው መኾኑን የገለጹት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ሌሎች ባለሃብቶችም በመሳተፍ በራስ አቅም መታከም የማይችሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ማገዝ ይገባቸዋል ብለዋል።

በጤና መድኅን የታየውን መሻሻል በከተማ አሥተዳደሩ የሚገኙ ሁሉም ተቋማት እንደተሞክሮ ሊወስዱት ይገባልም ነው ያሉት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ሰላም እና ልማት የትብብር ውጤት ነው” አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)
Next articleበ2018 በጀት ዓመት ካለፈው በላቀ ለመሥራት እና የከተማዋን ሰላም ለመጠበቅ በሰፊው ታቅዷል።