በምሥራቅ አማራ ባሉ ከተሞች እየተሠሩ ያሉ መሠረተ ልማቶች ያሉበትን ደረጃ የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች እየጎበኙ ነው፡፡

343

ምልከታ የተደረጉባቸው ከተሞች የሰቆጣ፣ ላልይበላና ወልድያ ከተሞች ናቸው፡፡ በክልሉ፣ በከተሞችና በዓለም ባንክ በጀት የተሠሩ የ2012 በጀት ዓመት መሠረተ ልማቶች ግንባታዎች ናቸው በመሪዎቹ የተጎበኙት፡፡

በሰቆጣ ከተማ አስተዳደር የጌጠኛ ድንጋይ መንገድ ንጣፍ፣ ድልድይ፣ የገበያ ማዕከል የአጥር ግንባታ ሥራዎች ያሉበት ደረጃ ተጎብኝቷል፡፡ ከተማዋ በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ ውስጥ መግባት መቻሏ ከዚህ ቀደም ይሠሩ ከነበሩ መሠረተ ልማቶች በተሻለ ሰፋ ያሉ ፕሮጀክቶችን እንድታከናውን እንዳስቻላት ምክትል ከንቲባ አሸብር ግርማይ ተናግረዋል፡፡ በበጀት ዓመቱም በ33 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጭ 25 ፕሮጀክቶችን ለመሥራት ዕድል መፍጠሩንም ነው የተናገሩት፡፡ ፕሮጀክቶቹ በተደራጁ የከተማዋ ወጣቶችና ተቋራጮች እየተሠሩ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ “አብዛኞቹን ፕሮጀክቶች በጥራት ለመፈጸም ጥረት ተደርጎ ነበር” ያሉት አቶ አሸብር የተስተዋሉ የጥራት መጓደሎች እንዲስተካከሉ ባሉት ቀናት በትኩረት እንሠራን ብለዋል፡፡

በክልሉ ከተማ ልማትና ቤቶች ኮንስትራክሽን ቢሮ የከተሞች ተቋማዊ መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ኃላፊ አሻግሬ አቤልነህ በሰጡት አስተያየት የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር የመሠረተ ልማቶችን ግንባታ በጊዜ ጀምሮ በጊዜ ማጠናቀቅ ለሌሎች አርዓያ መሁኑን ገልጸዋል፡፡ የተሠሩ መሠረተ ልማቶች ጥሩ ደረጃ ላይ ቢሆኑም የተስተዋሉ አንዳንድ የጥራት መጓደሎች ግን መስተካከል እንደለባቸው አቅጣጫ መቀመጡን ነው የተናገሩት፡፡

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ክፉኛ የቱሪስት እንቅስቃሴዋን ያቀዘቀዘባት የላልይበላ ከተማ አስተዳደርም የጉብኝቱ አካል ነበረች፡፡ የጌጠኛ ድንጋ መንገድ ንጣፍ፣ ድልድይ፣ የውኃ ማፈሰሻ ቦዮችን ጨምሮ በሆቴልና ኢንቨስትመንት እየተሠሩ ያሉ ግንባታዎች እንዲሁም የቅርስ ቦታዎች ተጎብኝተዋል፡፡
በከተማዋ በበጀት ዓመቱ በ 32 ሚሊዮን ብር ወጭ 22 አዳዲስ ፕሮጀክቶችንና 4 የጥገና ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ ነው ወደ ሥራ የተገባው፡፡ የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ማንደፍሮ ታደሰ “ሥራችንን ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ እየሠራን ቢሆንም ከተማዋ ካላት ወጣ ገባ ገጽታ አንጻር በተመደበው ገንዘብ ፕሮጀክቶችን ለማስጨረስ የገንዘብ አቅም እክል ፈጥሮብናል” ብለዋል፡፡ ከፍታና ተዳፋታማ ባሕሪ ያላቸውን ፕሮጀክቶች ለመሥራት የሚጠይቀው ገንዘብና አቅም ከታቀደው በላይ ሆኖ መገኘቱ ነው የተናገሩት፡፡ ሥራዎቹም አብዛኞቹ 80 ከመቶ አካባቢ የደረሱ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

“የከተማዋ ወጣገባነት ለግንባታ አስቸጋሪ ነው” ያሉት ደግሞ በክልሉ ከተማ ልማትና ቤቶች ኮንስትራክሽን ቢሮ የከተሞች ተቋማዊ መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ኃላፊ አሻግሬ አቤልነህ ናቸው፡፡ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቁ የከተማ አስተዳደሩ ጥረት ማድረግ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

በወልደያ ከተማ አስተዳደርም የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ መንገድና የውኃ ማፋሰሻ ቦዮችን ጨምሮ ከዚህ ቀደም ተገንብቶ አሁን ላይ ለዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሮበት አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው የአረንጓዴ ልማትና የመዝናኛ ቦታም የጎብኝቱ አካል ነበሩ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ሙሐመድ ያሲን በበጀት ዓመቱ በ98 ሚሊዮን ብር ወጭ 51 ፕሮጀክቶችን ለመሥራት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን አስታውቀዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ የተሠሩ ዋና ዋና መሠረተ ልማቶችንም በተያዘላቸው ጊዜ እንደሚያጠናቅቁ ነው ያስታወቁት፡፡

ዘጋቢ፦ ይርጋዓለም አስማማው

Previous articleበኩር ጋዜጣ ግንቦት 24/2012 ዓ/ም ዕትም
Next articleሁለት የራያ ቆቦ ወረዳ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ህግ በማስከበር ላይ እያሉ ሕይወታቸው አለፈ።