
ደሴ ፡ ሰኔ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴንን(ዶ.ር) ጨምሮ የደቡብ ወሎ ዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከወግዲ ወረዳ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በዘላቂ የሰላም እና ልማት ዙሪያ መክረዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ ነዋሪዎች ታጣቂ ቡድኑ እያደረሰ ካለው ዘረፋ፣ ጠለፋ እና እገታ በላይ ልጆቻቸውን ከትምህርት ገበታ ውጭ ማድረጉን ነው የተናገሩት።
ነዋሪዎቹ ታጣቂው ቡድን የልጆቻቸውን ህልም አቀጭጮ ለሥነ ልቦና ችግር እና ስደት እንደዳረጋቸውም አንስተዋል።
በታጣቂ ቡድኑ የተሳሳተ መረጃ እና የሃሰት ፕሮፓጋንዳ የአካባቢያቸው ሰላም መደፍረሱን የተናገሩት ነዋሪዎቹ ቡድኑ እያደረሰባቸው ካለው ስቃይ ለመዳን የአካባቢያቸውን ሰላም ለመጠበቅ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ወሎ ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋ ዳኛው ዘላቂ ሰላምን እና ልማትን ለማረጋገጥ ማኅበረሰቡ አጥፊዎችን ለይቶ መታገል አለበት ብለዋል። ዘላቂ ሰላምን እውን ለማድረግ የሃይማኖት አባቶች ለእውነት ብለው ሊሠሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን ከኅብረተሰቡ ውስጥ ለጽንፈኛ ቡድኑ መረጃ እና ስንቅ የሚያቀብሉ በመኖራቸው የማኅበረሰቡ ስቃይ እና እንግልት እንዲራዘም ማድረጉን ነው ያስረዱት። ማኅበረሰቡ ከዚህ ድርጊት መታቀብ እንዳለበትም አሳስበዋል።
የሰላም እጦቱ በወግዲ ወረዳ እየተሠሩ ያሉ እና ሊሠሩ የታቀዱ ልማቶችን አደናቅፏል ያሉት አሥተዳዳሪው የሰላም አማራጭን አልቀበል ያለውን ጽንፈኛ ኀይል ኅብረተሰቡ ከመንግሥት ጎን ተሰልፎ በመታገል አካባቢውን እንዲጠብቅ አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) መንግሥት ዘላቂ ሰላም እና ልማትን እውን ለማድረግ የሰላም አማራጮችን አሟጦ እየተጠቀመ መኾኑን አስረድተዋል።
ከግጭት እና ከድህነት አዙሪት ለመውጣት የክልሉ መንግሥት የ25 ዓመት ዕቅድ አቅዶ ወደ ሥራ መግባቱን የገለጹት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ለዚህም መንግሥት እና ሕዝብ በጋራ ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።
ዶክተር አብዱ “ሰላም እና ልማት የትብብር ውጤት ነው” እንደኾኑም አንስተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን