
ባሕር ዳር: ሰኔ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በ2017 በጀት ዓመት የፓርቲ እና የመንግሥት ሥራዎች ዓመታዊ የማጠቃለያ ግምገማ እንዲሁም የቀጣይ 90 ቀናት እቅድ ኦሬንቴሽን መድረክ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የ2017 በጀት ዓመት ሥራ ሲጀመር በአንድ እጅ ሰላምን ለማረጋገጥ በሌላው እጅ ደግሞ በትልቁ አቅደን ለመሥራት ነበር፤ ሁለቱንም ዕቅዶች በሚገባ አሳክተናል ብለዋል።
አሁን ላይ በባሕር ዳር እና የአካባቢዋ ሰላም ሰፍኗል ያሉት አቶ ጎሹ እንዳላማው ከተማዋ ጽዱ፣ ውብ፣ አረንጓዴ፣ የቱሪዝም መዳረሻ እና የኢንዱስትሪ መናገሻ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
የኮሪደር ልማቱ የሥራ ባሕል ለውጥን በሚያመጣ መልኩ ተከናውኗል። በመኾኑም ከተማዋ ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ለጎብኝዎች የምትመረጥ እና ሃብት አመንጪ ከማድረግ ባሻገር የሰው ሃብትም ተገንብቷል ብለዋል።
እንደ ክልል እና ሀገር በአንድ ዓመት ውስጥ መሬትን አራት ጊዜ በሊዝ ለአልሚዎች ማስተላለፍ መቻሉን በስኬት ያነሱት አቶ ጎሹ በቀጣይም ለአምስተኛ ጊዜ የሊዝ ልዩ ጨረታ ተዘጋጅቶ ቀርቧል ነው ያሉት። ይህም የመሪዎችን ትጋት ያመላክታል ሲሉ ተናግረዋል።
የባሕር ዳር ከተማ እስካሁን ባካሄደችው ልማታዊ ሥራዎች ጎብኝዎችን ከማስደመሙ ባለፈ ጎብኝዎች ልምድ የሚቀምሩባት ውብ ከተማ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።
በከተማዋ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ተጀምረው የነበሩ 22 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገዶችን በአብዛኛው ተጠናቅቀዋል ያሉት አቶ ጎሹ በመሬት ዘርፍ እና በቴክኖሎጂ ረገድም በተለይ ዘመናዊ የሲሲቲቪ ካሜራዎችን ተክሎ በመጠበቁ ረገድ ጥሩ ሥራ ተከናውኗል።
አቶ ጎሹ አክለውም በጤና እና ትምህርት ዘርፎችም አበረታች ሥራዎች መከናዎናቸውን አንስተዋል።
መልካም አሥተዳደርን እና የአገልግሎት አሰጣጥን ፍትሐዊ እና ነጻ ከማድረግ አኳያ ውስንነት መኖሩን ያነሱት አቶ ጎሹ መሪዎች አበክረው መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። ባለሙያዎች ሙሉ ሰዓት የማሠራት እና የመገምገም ችግር መኖሩንም ተናግረዋል።
በቀጣይ ሦሥት ወራት ዕቅድም በመልካም አሥተዳደርን በማስፈን፣ በአገልግሎት አሰጣጥን ችግር በተለይ ጉቦ፣ ሙስና እና አድልኦ፣ ሕገ ወጥ የመሬት ወረራን በትግል ማስወገድ ያስፈልጋል ብለዋል።
ባሕር ዳር የበለጠ ውብ፣ ማራኪ ስማርት ከተማ ሊያደርጓት የሚያስችሉ አዳዲስ ዕቅዶች መያዛቸውን አቶ ጎሹ አስታውሰዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የፖለቲካ እና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ አቶ ጊዜው ታከለ እንዳሉት የባሕር ዳር ከተማ ነዎሪዎች ሰላም እንዲሰፍን፣ ሕግ እንዲከበር እና የመንግሥት መዋቅር እንዲጠናከር እና ልማት እንዲሻሻል ይፈልጋል። በመኾኑም ሕዝቡ በብሎክ እየተደራጀ ሰላሙን በመጠበቅ ሰላምን እያጸና መኾኑን ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን