
አዲስ አበባ: ሰኔ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጉድ ሳማሪታን ማኅበር አዘጋጅነት በቅብብሎሽ ሥርዓት ዙሪያ ከአጋር አካላት ጋር ምክክር ተካሂዷል።
በርካታ ኢትዮጵያውያን በሕገ ወጥ መንገድ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ እና ለሥራ ወደ ዉጪ ሀገራት ይጓዛሉ።
የዜጎች ግንዛቤ ባለመዳበሩ እና በቂ ሥልጠናዎችን ባለመውሰዳቸው ምክንያት በርካቶች ጉዟቸው እንዳሰቡት ሳይኾን ለከፋ ጉዳት የሚዳረጉበት ሁኔታ ሲከሰት ይስተዋላል።
የዚህ ችግር ገፈትን ከቀመሱት መካካል
ወደ ሱዳን ሀገር ተሰደው የነበሩ ከስደት ተመላሾች ገልጸዋል። በሀገሪቱ በተፈጠረዉ የሰላም እጦት ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን አስታውቀዋል።
ወደ ሀገራቸው ሲገቡ በትክክል መረጃችን ከመመዝገብ ጀምሮ ተገቢውን ክትትል እና ድጋፍ ከማድረግ አንፃር ችግሮች እንደገጠሟቸዉ ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት በርካቶች ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን አንስተዋል።
ከዚህ ችግር እንዲወጡ ጉድ ሳማሪታን ማኅበር በመጠለያ ተቀብሎ ሥልጠና፣ ሕክምና እና የሥራ ማስጀመሪያ ካፒታል ቢሰጣቸውም የተደራጀ የመረጃ ቅብብሎሽ ሥርዓት በአግባቡ ባለመተግበሩ አሁንም በችግር ውስጥ መኾናቸውን ከስደት ተመላሾቹ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ሥራ እና ክህሎት ቢሮ የውጭ ሀገራት ሥራ ስምሪት ቡድን መሪ ሳሙኤል ግርማ የቅብብሎሽ ሥርዓት የሚደነግግ አዋጅ እና መመሪያ ቢኖርም በትክክል ወደ ሥራ እንዳይገባ የግንዛቤ ችግር መኖሩን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮ በሰው መነገድ እና ሰዎችን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል መከላከል ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አቃቤ ሕግ የኾኑት መኪያ ዲኑ ሀገሪቱ ከስደት ተመላሾችን መልሶ ማደራጀት የሚያስችል አዋጅ ቢኖራትም የተደራጀ የመረጃ ቅብብሎሽ ሥርዓትን ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር ተቋማት ወጥ አተገባበር እንደሌላቸው አስታውቀዋል። ይህን ችግር ለመፍታት ግንዛቤን ማዳበር ይገባል ብለዋል።
የጉድ ሳማሪታን ማኅበር የፕሮግራም ማኔጀር እታፈራሁ ሰመረ አጋር አካላት በአዋጁ እና መመሪያዎች ላይ በቂ መረጃ እና ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማኅበሩ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየሠራ መኾኑን አስታውቀዋል። ማኅበሩ የጀመረውን የተቀናጀ እና የዳበረ የቅብብሎሽ ሥርዓትን መከተል ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ:- ኢብራሂም ሙሃመድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን