ከ114 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል።

17

ባሕር ዳር: ሰኔ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ የ2017 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በፍኖተ ሰላም ከተማ አካሂዷል።

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህ የሀገርን የወደፊት እጣ ፋንታ የሚወስነውን ችግኝ ተከላ ሁሉም በባለቤትነት በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። በተለይም ችግኞችን ከመትከል ባለፈ የጽድቀት መጠናቸው ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በዚህ ዓመት የደን፣ የአትክልት እና ፍራፍሬ 114 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል እየተሠራ መኾኑን የምዕራብ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ አጉማሴ አንተነህ ገልጸዋል።በዚህ ዓመት ከሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በአንድ ቀን ጀምበር ወደ 500 ሺህ የሚጠጉ ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን አቶ አጉማሴ ተናግረዋል።

እስካሁን በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የጽድቀት መጠን 83 በመቶ መድረሱን እና ወደ 95 በመቶ ለማሳደግ እየተሠራ ነው ብለዋል። በከተማው ከ569 ሺህ በላይ ችግኞችን ለመትከል እየተሠራ መኾኑን የፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መንገሻ እንኳኾነ ተናግረዋል።

በዞኑ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሩ የአካባቢን ሥነ ምኅዳር ከመጠበቅ ባለፈ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ባላቸው ችግኞች ላይ ትኩረት በማድረግ እየተሠራ በመኾኑ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መኾናቸው ተገልጿል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ኢትዮጵያ እንደ ባሕር ትልቅ ሀገር ናት፤ በትናንሽ ጠጠር አትታወክም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleያለ አሽከርካሪ የሚጓዘው መኪና!