“ኢትዮጵያ እንደ ባሕር ትልቅ ሀገር ናት፤ በትናንሽ ጠጠር አትታወክም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

35

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄ እና አስተያየቶች ምላሽ እና ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል።

ዲፕሎማሲን በተመለከተ ለተነሳላቸው ጥያቄ ማብራሪያ ሲሰጡ ዓለም ኢ-ተገማች በኾነ መንገድ ነው እየተጓዘ ያለው፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ እንደኛ ዓይነት ድሃ ሀገር ጥንቃቄ የተሞላበት ጉዞ ያስፈልገዋል ብለዋል። ያሉንን ወዳጆች በመጠበቅ፤ የማይወዱንን ደግሞ በማለዘብ ሚዛን ጠብቀን ነው የምንጓዘው ሲሉ ተናግረዋል።

የዓለምን ሁኔታ በንቃት መከታተል በዚያ ውስጥ ደግሞ የሀገርን ጥቅም ማስከበር ይገባል ነው ያሉት። ከጎረቤት ውጭ ኢትዮጵያ ሕልውና አይኖራትም፤ ከኢትዮጵያ ውጭም እነሱ ህልውና የላቸውም፤ አንዳችን ለሌላችን በጣም አስፈላጊ ነን ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ግልጽ ድንበር አልተበጀላትም፤ ከሁሉም ጋር አከራካሪ ነው፣ ድንበር በደንብ አልተለየም፣ የንግድ ሥርዓቱም አከራካሪ ነው፣ ይህም ልክ እንደማንኛውም እዳ የወረስነው ነው ሲሉ ተናግረዋል። ግልጽ ድንበር እና ግንኙነት ኖሮን ሳይኾን ሳይፈቱ ያደሩ ጉዳዮች ነበሩ፤ ይህም በሂደት እና በመልካም ግንኙነት እንዲፈታ ይሠራል ብለዋል።

የቀይ ባሕር ወደብ ባለቤትነትን በተመለከተም በሰላም እና በሰላማዊ የንግድ ሥርዓት መሠረት እንነጋገራለን ብለዋል። ጊዜውን ጠብቆ ፍሬ እንደሚያፈራም ገልጸዋል። በግጭት እና በኃይል ግን አናደርግም ብለዋል። ግጭት ለማንም አይጠቅምም፤ ኢትዮጵያ ሰላም ከሌላት በኢኮኖሚ የተሳሰሩ ጎረቤቶቿ የበለጠ ተጎጅዎች ናቸው ነው ያሉት።

የሀገራትን ሉዓላዊነት እናከብራለን፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር ካላገኘች ሉዓላዊ ሀገር መኾን እንደማትችልም ደግሞ ሌሎች ማወቅ እና ማመን እንዳለባቸውም ጠቅላይ ሚኒስትትሩ አስገንዝበዋል። አብሮ ለመኖር ሰጥቶ መቀበል ያስፈልጋል ብለዋል። በመነጋገር ኢትዮጵያ የባሕር በር የምታገኝበትን መንገድ መፈለግ እንደሚያስፈልግም አስምረውበታል።

“ኢትዮጵያ እንደ ባሕር ትልቅ ሀገር ናት፤ በትናንሽ ጠጠር አትታወክም፤ ይህንን መገንዘብ ያስፈልጋል” ብለዋል። ኢትዮጵያ የሚያውኳትን እየተከላከለች መልማት የምትችል ትልቅ ሀገር ናት፤ የዘመነ ወታደር እና ቴክኖሎጅም የታጠቀች ሀገር ናት ብለዋል።

ከኤርትራ ጋር ውጊያ እንደሚነሳ አድርገው የሚያነሱ አሉ፤ ውጊያ ክፉ ነገር ነው፤ በኢትዮጵያ በኩል አንዲትም ጥይት አይተኮስም ብለዋል። ምክንያቱም ብዙ የሚያጓጉ የልማት ፕሮጀክቶች በእጃችን አሉ፤ መሥራት ነው የምንፈልገው ነው ያሉት። ከዚህም በላይ ኤርትራውያን፣ ሶማሊያውያን፣ ሱዳናውያንም ኾኑ ሌሎች ሕዝቦች ወንድም እና እህት ሕዝቦች ናቸው ተባብረን መሥራት እና ማደግ ነው የምንፈልገው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የኢትዮጵያን ማክበር እና ሰላም መፈለግ ግን በነሱም በኩል በምጥጥን እንዲያዩት እንፈልጋለን ነው ያሉት። ከሁሉም ጎረቤት ሀገሮች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ነበረን፤ ማስቀጠልም እንፈልጋለን ብለዋል። “ውጊያን አንመርጥም፤ ሰላም እና ትብብርን ብቻ ነው የምንፈልገው” ሲሉም ገልጸዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለኛ ብቻ አይኾንም፤ ወደ ኤርትራ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱማሊያ እና ወደ ሌሎችም እያስገባን በጋራ ማደግ ነው የምንፈልገው ብለዋል። በጋራ እየለማን በሰላም መኖር ዋነኛ ዓላማችን ነው፤ በሰላም የማያኖር ጉዳይ ከገጠመ ግን ራሳችንን እንከላከላለን እንጅ የሚያሰጋን ነገር የለም ሲሉ ገልጸዋል። “ኢትዮጵያ ራሷን ለመከላከል በቂ አቅም አላት” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየ2018 በጀት ዓመት በጀት 1 ነጥብ 93 ትሪሊዮን ብር ኾኖ ጸደቀ።
Next articleከ114 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል።